ኢትዮጵያና ኬንያ ሁለንተናዊ የትብብር ግንኙነታቸውን የበለጠ ለማጠናከር ተስማሙ

62
አዲስ አበባ ሚያዝያ 29/2010 ኢትዮጵያና ኬንያ ፖለቲካዊና ምጣኔ ኃብታዊ ጉዳዮችን ጨምሮ የአገሮቹን እድገትና ብልፅግና ሊያፋጥኑ በሚያስችሉ የትብብር መስኮች ያላቸውን ግንኙነት የበለጠ ለማጠናከር ከስምምነት ላይ ደረሱ። የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አቢይ አህመድ በኬንያ ለሁለት ቀናት ይፋዊ የሥራ ጉብኝት ባደረጉበት ወቅት መሪዎች ባወጡት የጋራ መግለጫ፤ በግብርና ልማት፣ በኢንቨስትመንት፣ በትራንስፖርት፣ በቱሪዝም፣ በወታደራዊና ፀጥታ ጉዳዮች እንዲሁም ሽብርተኝነትን ለመከላከል በትብብር ለመስራት መስማማታቸውን አስታውቀዋል። ከአይሲዮሎ - ሞያሌ - አዲስ አበባ የሚዘልቅ መንገድ እንዲሁም ከናይሮቢ አዲስ አበባ የሚደርስ የባቡር ትራንስፖርት ለመዘርጋት መስማማታቸውን በጋራ መግለጫቸው አመልክተዋል። በተጨማሪም የላሙ-ጋሪሳ-አይሲዮሎን እና የሞያሌ- ሀዋሳ-አዲስ አበባ መንገድ ፕሮጀክትን በጋራ ለመቆጣጠርና ለመከታተልም ከስምምነት ላይ መድረሳቸውን ገልፀዋል። የኬንያ መንግስት ኢትዮጵያ በላሙ ወደብ መሬት የምታገኝበትን ሁኔታ ለማመቻቸት ቃል የገባ ሲሆን፤ የኢትዮጵያ መንግስትም በበኩሉ በሚያገኘው መሬት ላይ የሎጂስቲክ እንቅስቃሴ መገልገያዎችን የሚያለማ መሆኑን አረጋግጧል። መሪዎቹ አክለውም ሁለቱ አገሮች የሚዋሰኑባትን ሞያሌ "የጋራ ከተማና የኢኮኖሚ እምብርት" ለማደረግ የሚያስችል ፕሮጀክት ለመንደፍም ተስማምተዋል። ለፕሮጀክቱ ልማት የሚያስፈልገውን ወጪ በጋራ ለመሸፈን የተስማሙ ሲሆን፤ ተጨማሪ ኃብት ከሌሎች አካላት በጋራ ለማፈላለግም ከስምምነት ላይ ደርሰዋል። የኢትዮጵያና ኬንያ የግሉ ዘርፍ አካላት አገሮቹን ተጠቃሚ የሚያደርጉ አዋጭ ዘርፎችን በመለየት እንዲሰማሩ ለማበረታታት፤ በመካከላቸው ያለው የንግድና ኢንቨስትመንት ድባብ ምቹ እንዲሆን የየበኩላቸውን ጥረት ለማድረግም ቃል ገብተዋል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አቢይና የኬንያ ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ በዚሁ የጋራ መግለጫቸው የጋራ ወታደራዊ ስልጠናዎችን ለማካሄድ እንደዚሁም የእስረኞች ልውውጥ ለማድረግ መስማማታቸውን አስታውቀዋል። መሪዎቹ በአሁኑ ወቅት ለአደጋ ተጋላጭ በሆኑ ማህበረሰቦች መካከል እየተባባሰ የመጣውን አለመግባባት በመፍታት ዘላቂ ሰላም ለማምጣት ለሚደረገው እንቀስቃሴ እንቅፋት ተብለው የተለዩ ተግዳሮቶችን ለመፍታት በድንበር አካባቢዎች ሁሉንም በሚያካትቱ የምጣኔ ኃብት ልማት ላይ ትኩረት ሰጥቶ መስራት እንደሚገባም ከስምምነት ላይ ደርሰዋል። የድንበር ላይ የንግድ ልውውጥን ማጠናከር በአካባቢው ያለውን ህዝብ ህይወት ለማሻሻል ከፍተኛ ሚና ያለው መሆኑም ተመልክቷል። አገሮቹ በአካባቢው ሰላም እንዲሰፍን በተለይም በጎረቤት ሶማሊያና ደቡብ ሱዳን አስተማማኝ ሰላምና ፀጥታ እንዲረጋገጥ ከአሁን በፊት እያደረጉት ያለውን የትብብር ጥረት ለማጠናከር ተስማምተዋል። በደቡብ ሱዳን ሰላም ለማምጣት የሚካሄደው ጥረት በመጓተቱ መሪዎቹ ማዘናቸውንም ገልፀዋል። የደቡበ ሱዳን የፖለቲካ አመራር አባላት ከራሳቸው ጥቅም ይልቅ የህዝብን ጥቅም በማስቀደም በአገሪቷ ሰላም እንዲመጣ የበኩላቸውን እንዲወጡ ሁለቱ መሪዎች አሳስበዋል። ኢትዮጵያና ኬንያ የደቡበ ሱዳን ሰላም እውን ይሆን ዘንድ በምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት (ኢጋድ) አማካኝነት እየተካሄደ ያለው የሰላም ድርድር ጥረት የተሳካ እንዲሆን ፅኑ አቋም ያላቸው መሆኑን አረጋግጠዋል። አል-ሻባብ የተባለው የሽብር ቡድን በሶማሊያና በአካባቢው አገሮች ላይ ስጋት መሆኑ እንደቀጠለ መሆኑን መሪዎቹ አመልክተዋል። የሶማሊያን ሰላም ለማረጋገጥ ዓለም ዓቀፉ ማህበረሰብ በቀጠናው ለተሰማራው የአፍሪካ ህብረት ሰላም ማስከበር ተልዕኮ (አምሶም) የሚያደርገው ድጋፍ በቂ አለመሆኑ ውጤቱ አመርቂ እንዳይሆን ማድረጉንም ገልጸዋል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም