በአማራ ክልል መድኃኒት የሚያቋርጡ ሰዎች የቲቢ በሽታ እንዲስፋፋ እያደረጉ ነው...የክልሉ ጤና ቢሮ

116

ባህር ዳር  መጋቢት 26/2011 በአማራ ክልል የቲቢ በሽታ ሕክምናቸውን የሚያቋረጡ ሰዎች መድኃኒቱ የተላመደ የቲቢ በሽታ እንዲስፋፋ እያደረጉ መሆኑን የክልሉ ጤና ቢሮ አስታወቀ።  

በቢሮው የቲቢፕሮግራም ኬዝ ቲም አስተባባሪ አቶ ገብሬ ሙሴ ለኢዜአ እንደገለጹት መድኃኒቱን የተላመደ የቲቪ በሽታ እየተስፋፋ መምጣት በክልሉ ዋነኛ የጤና ችግር እየሆነ ነው።

በቲቢ በሽታ ከተያዙት ሰዎች የተወሰኑት በመጀመሪያ ስድስት ወራት የሚሰጠውን ሕክምና በማቋረጣቸው ለከፋ ችግር እየተጋለጡ መሆናቸውን ተናግረዋል።

አስተባባሪው እንዳሉት መድኃኒቱ ከሚያስከትለው የጎንዮሽ ጉዳት ጋር ተያይዞ የታዘዘላቸውን መድኃኒቱን ወስደው የሚጨርሱት ከ75 እስከ 80 በመቶ የሚሆኑ ሕሙማን ብቻ ናቸው።

ቀሪዎቹ ከ20 እስከ 25 በመቶ የሚሆኑት መድኃኒቱን ጀምረው የሚያቋርጡ መሆናቸውን በማሳያነት ገልጸዋል።

መድኃኒቱን በተላመደ ቲቢ በሽታ የተያዙ ሰዎች ተኝተው የሚታከሙባቸው ሆስፒታሎች ቁጥር አናሳ መሆን፣ የትራንስፖርት ችግርና የምግብ ድጋፍ ማነስ መድኃኒት ለማቋረጥ ምክንያት መሆናቸውንም አስረድተዋል።

"ሕሙማን መድኃኒት በማቃረጥ ለከፋ የጤና ችግርና ለሞት እየተዳረጉ ይገኛሉ" ብለዋል።

በአጭር ጊዜ ታክሞ መዳን ሲቻል ሕሙማን ሕክምናቸውን በማቋረጣቸው መድኃኒቱን ለተላመደ የቲቪ በሽታ እየተጋለጡ ከሁለት እስከ ሦስት ዓመት የሚፈጅ ሕክምና ለመውስድ እየተገደዱ መሆኑንም አመልክተዋል።

በክልሉ በፀበል ቦታዎች፣ በማረሚያ ቤቶች፣ በሜጋ ፕሮጀክቶች፣ በትምህርት ተቋማትና በህጻናት ማሳደጊያ ቦታዎች በርካታ ሰዎች ከመኖራቸው ጋር ተያይዞ ለበሽታው የመጋለጥ ዕድሉ ሰፊ መሆኑ ገልጸዋል።

እንደአቶ ገብሬ ገለጻ መድኃኒቱን በተላመደ ቲቢ በሽታ የሚጠይቀው ወጭ ከባድ በመሆኑ እስካሁን በክልሉ ሕክምናው እየተሰጠ ያለው ከግሎባል ፈንድ በዕርዳታ በተገኘ መድኃኒት ነው።

ባለፈው ዓመት የመጀመሪያ ግማሽ ዓመት በክልሉ መድኃኒቱን በተላመደ ቲቢ በሽታ የተያዙት 65 ሰዎች ሕክምና እንደተሰጣቸው ገልጸው በተያዘው ግማሽ ዓመት ደግሞ የሕሙማኑ ቁጥር ወደ 85 ከፍ ማለቱን አስረድተዋል። 

"ችግሩን በዘላቂነት ለመከላከል የሕብረተሰቡን ግንዛቤ ከማሳደግ ጎን ለጎን በበሽታው የተያዙትን ፈጥኖ ወደህክምና ተቋም በማምጣት ሕክምናቸውን ተከታትለው እንዲጨርሱ ለማድርግ ቢሮው ከአጋር አካላት ጋር በትብብር እየሰራ ነው" ብለዋል።

በባህር ዳር ፈለገ ሕይወት ስፔሻላይዝድ ሪፈራል ሆስፒታል የቲቢ ሕክምና ክፍል ባለሙያ አቶ ምንይችል ባንቴ በበኩላቸው መድኃኒቱን ለተላመደ ቲቢ በሽታ በሆስፒታሉ ክትትል የሚያደርጉ ሕሙማን መኖራቸውን ጠቁመዋል።

በቲቢ በሽታው የተያዘ ሰው የሚሰጠውን የመጀመሪያ ሕክምና በአግባቡ ካልጨረሰ መድኃኒቱን ለተላመደ የቲቢ በሽታ እንደሚዳረግም ተናግረዋል።

"በቲቪ በሽታ መያዙን በሕክምና ያረጋገጠ ሰው በሽታው ወደሌላው ሰው እንዳይተላለፍ በኃላፊነት ስሜት መጠንቀቅ ይኖርበታል" ሲሉም ገልጸዋል።

ከአንድ ዓመት በፊት የመጀመሪያውን የቲቢ ሕክምናውን በማቋረጡ ለተላመደ የቲቪ በሽታ መዳረጉን የተናገረው ደግሞ በባህር ዳር ከተማ የሚኖረው ወጣት ምንይችል ዓለም ነው።

"በተላመደ የቲቪ በሽታ መያዜን ካወቅኩ ጀምሮ በሽታው ወደሌሎች ሰዎች እንዳይተላለፍ ጥንቃቄ እያደረኩ ነው" ያለው ወጣቱ መድኃኒቱን መውሰድ ከጀመረ አንድ ዓመት እንደሆነው ተናግሯል።

የቲቢ በሽታ ታማሚ እንደሆነ በቅርቡ ማወቁን የገለጸው ሌለው የእዚሁ ከተማ ነዋሪ ወጣት አብርሃም ሰማ ነው።

ስለበሽታውና መደረግ ስላለበት ጥንቃቄ በሕክምና ባለሙያዎች ግንዛቤ በማግኘቱ ለመጀመሪያ ጊዜ የሚሰጠውን የቲቪ በሽታ ሕክምና በአግባቡ እየተከታተለ መሆኑን ተናግሯል።

ባለፈው ዓመት በክልሉ በመደበኛው የቲቢ በሽታ የተያዙ ከ22ሺህ 100 በላይ ሰዎች ታክመው የዳኑ ሲሆን በያዝነው በጀት ዓመት አጋማሽም ከ11 ሺህ የሚበልጡ ሰዎች ሕክምና እንዲያገኙ መደረጉን ከቢሮው የተገኘው መረጃ ያስረዳል ሲል የዘገበው ኢዜአ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም