ኢትዮጵያዊ አንድነትን በማጎልበት ሀገሪቱን ከገባችበት ቀውስ ማዳን ይገባል- አስተያየት ሰጪዎች

89

መጋቢት 26/2011 ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ወደ ስልጣን ከመጡ ወዲህ ባለው አንድ ዓመት ውስጥ መልካም ነገሮች ቢከናወኑም አሁንም በርካታ ችግሮች መኖራቸውን አስተያየት ሰጪዎች ተናገሩ።

ተማሪ እታገኝ ጭምዴሳ ባለፈው አንድ ዓመት ውስጥ የኢትዮጵያና የኤርትራን መታረቅ፣ ታስረው የነበሩ ዜጎች መፈታትና አንጻራዊ የሀሳብ ነጻነት መገኘቱን አንዱ የለውጥ ማሳያ ነው ብላለች።

ሀገራዊ ለውጡ እንደተጀመረ አካባቢ ኢትዮጵያዊ የሀገር ፍቅር እየጨመረ ነበር ያለችው ተማሪ እታገኝ ፤ ሆኖም የሀገር ፍቅር ከንግግር ባለፈ በተግባር በዘላቂነት ባለመታየቱ  ሀገሪቱ ችግር ውስጥ  መውደቋን ገልጻለች።

ሀገራዊ ለውጥ በመላው ህዝብ ተሳትፎ እንደሚሳካ ያነሳችው ተማሪዋ፤ የስራ ባህልን ማሻሻል፣ የሀገር ፍቅርን በተግባር ማሳየትና ከፋፋይ ጉዳዮችን ማስወገድ እንደሚገባ ነው የጠቆመችው።

ባለፈው አንድ ዓመት ሀገራዊ ለውጡ በሚፈለገው ልክ መሬት ላይ አልተተገበረም ያለው የደብረታቦር ዩኒቨርሲቲ የተማሪዎች ህብረት ተወካይ መንበሩ ነበረ፤ ለዚህም ምክንያቱ “የአስመሳይ አመራሮች መበራከት ነው” ብሏል።

ህዝቡ ትናንት ሲያነሳቸው የነበሩ ጥያቄዎችን የሚያፍኑ አመራሮች “በስመ ተደማሪነት” እርምጃ እየተወሰደባቸው አለመሆኑ ሀገራዊ ለውጡን ፈተና ላይ ጥሎታል ነው ያለው።

ኢትዮጵያዊ አንድነት አሁንም በተግባር እየታየ አለመሆኑ ለሀገራዊ ለውጡ ፈተና እንደሆነ ጠቅሶ፤ የሀገር ፍቅርን የሚሸረሽሩ ከፋፋይ ሀሳቦችና ግጭቶች ዜጎች መፈናቀላቸውን ገልጿል።

የአዲስ አበባ ነዋሪ አቶ ስለሺ መለሰ እንዳሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ወደስልጣን ከመጡ ጊዜ ጀምሮ ያለው ለውጥ አካሄዱ መልካም ቢሆንም በተቃርኖ የቆሙ ሃይሎች ዛሬም መኖራቸው መንገዱን ምቹ እንዳይሆን አድርገውታል።

ወጣቶችን፣ ሽማግሌዎችን፣ ሴቶችን፣ ምሁራንን፣ ፖለቲከኞችን የሚያግባባ የለውጥ ጉዞ ካልተደረገ አሁን ያሉት ችግሮች እየተባባሱ እንደሚሄዱም ስጋታቸውን ተናግረዋል።

“ሮም በአንድ ቀን አልትገነባችም፤ ሀገራዊ ለውጡም በአንድ ዓመት  ሁሉንም ነገሮች እንዲያሳካ መጠበቅ ሞኝነት ነው፤ ብዙ የተሰሩ መልካም ስራዎችም ችግሮችም አሉ” የሚሉት ደግሞ አቶ ታሪኩ ተሰማ ናቸው።

ዘረኝነት ለ27 ዓመታት በመሰበኩ አሁን ይፋዊ የሀገሪቱ ችግር መሆኑን ያነሱት አቶ ታሪኩ ኢትዮጵያዊነት ፈተና ውስጥ መውደቁን ተናግረዋል።

ተፎካካሪ  ፓርቲዎች የሚያወጧቸው መግለጫዎች ህዝብን ወደ መቃቃር እያስገቡ፣ ከኢትዮጵያዊ አንድነት ይልቅ በተከፋፈለ ጠርዝ እንዲቆም እያደረጉ ነው ብለዋል።

በፌስቡክ መረጃዎች ምክንያት ኢትዮጵያዊነት ዝቅ፣ ጎጠኝነት እየሰፋ መሆኑን ገልጸው፥  አደጋው የከፋ በመሆኑ ሀገሪቱን መታደግ የሚፈልግ አካል ቆሞ እንዲያስብም  ጠይቀዋል።

ተማሪ እታገኝ በቀጣይ በደልን ይቅር ተባብሎ ለቀጣይ የተሻለች ሀገር መስራት ይገባል ነው ያለችው።

የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች በብሔር ተከፋፍለው ድንጋይ ከመወራወር ይልቅ በተሰማሩበት የትምህርት ዓላማ  በመትጋት ለሀገራቸው መድረስ እንደሚገባቸውም ተናግራለች።

ኢትዮጵያ ውስጥ መከፋፈልንና ሞትን እየደገሱ የራሳቸውን ጥቅም የሚያግበሰብሱ ሃይሎች ላይ መንግስት ተገቢውን ቁጥጥር እያደረገ አለመሆኑን ጠቅሳለች።  

የፖለቲካ ንግድ ላይ የተሰማሩ ወገኖች ከግል ጥቅማቸው በፊት ሀገራዊ አንድነትን ማስቀደም ይገባቸዋልም ነው ያለችው።

ተማሪ መንበሩ በበኩሉ የታችኛው የመንግስት መዋቅር አገልግሎት አሰጣጥን ጨምሮ የህዝብን ጥያቄ እየመለሰ ባለመሆኑ መንግስት በፍጥነት እርምጃ ወስዶ ማስተካከል ይገባል ብሏል።

ህብረተሰቡን የሚያወናብዱ ሃይሎች ከመጥፎ ድርጊታቸው ተቆጥበው ሀገርን መታደግ የሚያስችሉ ሀሳቦችን በማቅረብ  የለውጡ ጉዞ ተሳታፊ እንዲሆኑ ጠይቋል።

“በየወረዳው ያሉ አመራሮች የጠቅላይ ሚኒስትሩን ስም በማስተጋባት ፎቶ ግራፉን በየቢሮው በመለጠፍ ለውጥ እያካሄድን ነው የሚል አፋዊነት ላይ ብቻ ተቀምጠዋል፤ ከዚህ ወጥተው ህዝቡን ማገልገል አለባቸው” ነው ያለው።

መንግስት ፈጣን ስራዎችን እንዲሰራ ህዝባዊ ድጋፍ ያስፈልገዋል ያለው ተማሪ መንበሩ፤ ለአንዲት ሀገር ሁሉም የበኩሉን የሚወጣበት ብሔራዊ መግባባት እንደሚያስፈልግም አንስቷል።

እታገኝ በበኩሏ  “ሀገር የምትጠፋው በአላዋቂዎች ጩኸትና በአዋቂዎች ዝምታ ነው። ሀገሪቱ ስጋት ላይ ወድቃለች ስለዚህ ታላላቅ ምሁራን የአላዋቀዊቹን ከፋፋይ ሀሳብ ለማስቆም የራሳቸውን ጠንካራ ሀሳብ ማጋራት መጀመር አለባቸው” ብላለች።

አቶ ስለሺ ደግሞ ከወረዳ እስከ ፌደራል ሁሉም በተቀናጀ መልኩ ከሰራ እና ህዝቡም ማንነቱን ጠብቆ ኢትዮጵያዊ አንድነቱን ካጎለበተ ስኬቶች ይመዘገባሉ ነው ያሉት።

ኢትዮጵያ ገናና ስሟ እንዲመለስ መንግስት ህግን ማስከበር እንዳለበት ዜጎችም ጠንክረው መስራት እንደሚገባቸውም ገልጸዋል።

ኢትዮጵያን ጫፍና ጫፍ ቆሞ እየጎተታት ያለውን ዘረኝነትን በማስወገድ፤ ሁሉም ዜጋ በማንኛውም የሀገሪቱ ክፍል ሰርቶ ተዋዶ የመኖር መብቱ  መከበር አለበት ነው ያሉት።

ሙሰኛ አመራሮች ካልተወገዱ እድገት፣ ሀገራዊ አንድነት አይታሰብም ያሉት አቶ ስለሺ፤  የህግ የበላይነት ሲተገበር ከአመራሩ መጀመር አለበት ብለዋል።

አቶ ታሪኩ “እንኳን አዲስ አበባ ሞያሌ፣ መቀሌ፣ ሌሎች ከተሞችም የመላው ኢትዮጵያውያን ናቸው፤ ብጥብጥ ፈጥሮ ለመጠቀም ‘ያ የኔ ነው ይህ የኔ ነው’ የሚሉ ሃይሎች ከድርጊታቸው ተቆጥበው ለኢትዮጵያ ሁለንተናዊ ለውጥ ይስሩ” ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

ስርዓት አለብኝነት የሚፈጥሩ አክቲቪስቶች፣ ፖለቲከኞች የመንግስት አመራሮች በህግ ሊጠየቁና  ስርዓት ሊይዙ  ይገባልም ነው ያሉት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም