መንግስት ለግጭት መንስኤዎች የማያዳግም የመፍትሔ እርምጃ እንዲወስድ የቴፒ ነዋሪዎች ጠየቁ

69

ሚዛን መጋቢት 25/2011 መንግስት ለግጭት መከሰት መንስኤ ለሆኑ ጉዳዮች የማያዳግም የመፍትሔ እርምጃ እንዲወስድ  በሸካ ዞን የቴፒ ከተማ ነዋሪዎች ጠየቁ፡፡

ነዋሪዎቹ በአካበቢው የተከሰተውን ግጭት ለመፍታት በቅርቡ ከተቋቋመው ኮማንድ ፖስት ጋር  ዛሬ በቴፒ ከተማ ተወያይተዋል።

ከውይይቱ ተሳታፊ ነዋሪዎች መካከል  አቶ ሀብታሙ ዓለሙ እንዳሉት የአካባቢው የጸጥታ ችግር ከለውጡ ወዲህ የመጣ ሳይሆን ለበርካታ ዓመታት የዘለቀ ነው።

ባለፉት ዓመታት በተከሰቱ ተደጋጋሚ ግጭቶችም የበርካታ ዜጎች ሕይወት ማለፉንና  በችግሩ ምክንያት የአካባቢው ማህበረሰብ በስጋት እንዲቆይ መድረጉን አመልክተዋል።

የንብረት ጥፋትን ጨምሮ ችግሩ አሁንም መቀጠሉን ተናግረው በከተማው እየደረሰ ካለው ጉዳት አንጻርም መንግስት የችግሩን አሳሳቢነት በመገንዘብ ዘላቂ መፍትሄ እንዲሰጠው ጠይቀዋል።

መንግስት ሠላምን ለማረጋጥ ያቋቋመው ኮማንድ ፖስት በጥንቃቄ ሊመራ እንደሚገባ ያመለከቱት ደግሞ  አቶ ይርጋ ሻሽ ናቸው።

በቴፒ  ከተማም ሆነ ሌሎች አካባቢዎች እየተፈጠሩ ላሉ የጸጥታ ችግሮች የመንግስት አመራሩ ሚና ሊጤን እንደሚገባም ጠቁመዋል።

አስተያየት ሰጪው እንዳሉት መንግስት የህዝብ አገልጋዮችን ከጸረ ሰላም አካላት ሊለይ እንደሚገባና ጥፋተኞችንም ተጠያቂ ማድረግ አለበት፡፡

በተደጋጋሚ የሚፈጠረውን የጸጥታ ችግር በዘላቂነት እንዲፈታም የግጭቱ መሠረታዊ ምክንያቶችን መለየት ሲቻልና ሕዝቡ ለሚያነሳው ጥያቄም ፈጣን ምላሽ ሲሰጥ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ሌላኛዋ የከተማዋ ነዋሪ ወይዘሮ ገበያነሽ መንገዱ በበኩላቸው " ከተማችንና አካባቢያችንን ከግጭትና ብጥብጥ ነጻ የሚሆንበትን ጊዜ እንሻለን" ብለዋል።

መንግስት ዋስትና ያለው ሰላምና ደህንነት እንዲያሰፍንላቸውም ጠይቀዋል።

በምዕራብ ዕዝ የ12ኛ ክፍለጦር ምክትል አዛዥና የኮማንድ ፖስቱ ሰብሳቢ ኮሎኔል ተስፋይ ሊላይ በበኩላቸው" ኮማንድ ፖስቱ የተቋቋመው ህገመንግሥታዊ ስርዓቱን ለማስከበር ፣  የዜጎችን ሰላምና ጸጥታ ለማረጋገጥ ነው" ብለዋል።

በቀጣይ አንድ ወር ኮማንድ  ፖስቱ በተቋቋመባቸው ካፋ ሸካና ቤንች ማጂ ዞኖች የተፈናቀሉ ዜጎች ወደቀድሞ ቀያቸው የማስመለስ እና ጥፋተኞችን የመያዝ  ስራ እንደሚከናወን ገልጸዋል።

የህግ የበላይነትን ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረትም የህዝቡ ትብብር እንደሚያስፈልግም አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም