የሶዴፓ የለውጥ እንቅስቃሴ የሚደገፍ መሆኑን የኢህአዴግ ሊቀመንበር ዶክተር አብይ አህመድ ገለጹ

69

ጅግጅጋ መጋቢት 25/2011 የሶማሌ ዴሞክራሲ ፓርቲ /ሶዴፓ/   የለውጥ እንቅስቃሴ የሚደገፍ መሆኑን የኢህአዴግ ሊቀመንበር ዶክተር አብይ አህመድ ገለጹ፡፡

ዶክተር አብይ ጂግጂጋ ከተማ ሲካሄደ በቆየው የሶዴፓ ድርጅታዊ ጉባኤ ማጠቃለያ ላይ ተገኝተው ባደረጉት  ንግግር  የክልሉን መንግስት የሚመራው የፓርቲው አዲስ አመራሮች ህዝቡ የሚፈልግባቸውን ውጤት ማስመዝገብ እንደሚጠበቅባቸው አመልክተዋል፡፡

"የክልሉ የተማሩ የፓርቲ አመራሮች የጎሳ ልዩነቶቻቸውን ማስወገድ አለባቸው" ብለዋል

የሶዴፓ የለውጥ እንቅስቃሴ  የሚደገፍ መሆኑን  ገልጸው ፓርቲው በድርጅታዊ ጉባኤው ላሳለፋቸው ውሳኔዎች ተግባራዊነት ከአባላቱና ከመላው ህዝብ ጋር መስራት እንደሚገባም ጠቁመዋል፡፡

" የፓርቲው ጉባኤ የኢትዮጵያ ሶማሌ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ የሚለውን ስያሜ መቀየሩ ትክክለኛና አዲስ ምዕራፍ ነው" ያሉት ዶክተር አብይ  የመገናኛ ብዙሃንም ከአሁን በኋላ  በአዲሱ ስያሜ እንዲጠቀሙ መዕልክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

" የዚህ ጉባኤ ውጤት በፓርቲው ታሪክ በአብዛኛው ምሁራን በመሪነት እንዲሳተፉ ማድረጉ ሁለንተናዊ ለውጥ ተደርጎ ይወስዳል " ብለዋል፡፡

ይህም የፌዴራል መንግስት በሶማሌ ክልል ያለው እምቅ የተፈጥሮ ሀብት ለማልማት የያዘውን እቅድ ለመተግበር የሚያስችል መሆኑን የኢህአዴግ ሊቀመንበር ዶክተር አብይ አህመድ አስታውቀዋል፡፡

ለኦብነግ አባላት የቢሮና ሌሎች አስፈላጊ ድጋፍ ሊደረግላቸው እንደሚገባ ጠቁመው እነሱም  የክልሉም ሆነ የሀገሪቱ ልማት ተሳታፊ እንዲሆኑ አመልክተዋል፡፡

በጉባኤው ማጠቃለያ መድረክ የተገኙት  ገራድ ኮልሚዬ ገራድ መሀመድ   የክልሉ ህዝብ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚመሩትን መንግስት  የሚደግፍ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

የኦብነግ ተወካይ አቶ ሁሴን ኑር በበኩላቸው ግንባሩ ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር የደረሰውን ስምምነት ለመተግበር  እንደሚሰራ ገልጸዋል፡፡

" በዚህ አደራሽ ኦብነግ ተገኝቶ  በሰላም ሀሳቡን  እንዲገልጽ መደረጉ  ጠቅላይ ሚኒስቴሩ የወሰዱት የለውጥ እርምጃ  አካል በመሆኑ  ጠቅላይ ሚኒስትሩን ከልብ እናመሰግናለን "ብለዋል ።

በጉባኤው ማጠቃለያ ስነስርዓት ለዶክተር አብይ አህመድና  ለአቶ ንጉሱ ጥላሁን የተዘጋጀላቸውን የሶማሌ ባህላዊ አልባሳት አቶ አህመድ ሼዴና አቶ ሙስተፌ መሐመድ አልብሰዋቸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም