የኢትዮጵያ መንግስት የአንድ አመቱ የሰብአዊ መብት አያያዝ በሂውማን ራይትስ ዎች እይታ

73


ሞኒተሪንግ/ኢዜአ /

ሂውማን ራይትስ ዎች (HRW) የተባለው አለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ተቆርቋሪ ተቋም በሃገራችን የሚስተዋለውን የሰብአዊ መብቶች አከባበር ሁኔታን አስመልክቶ በተለያዩ ጊዜያት ሪፖርቶችን ሲያወጣ ቆይቷል። ተቋሙ ባለፉት አመታት በሃገራችን የታዩትን የሰብአዊ መብት አያያዝን አስመልክቶ ያወጣቸው የነበሩ ሪፖርቶች መረጃን ተንተርሰው የሚቀርቡና አሉታዊ ይዘትን የተላበሱ ነበሩ። ይኸው የሰብአዊ መብቶች ተቆርቋሪ ተቋም ‘Abiy’s First Year as Prime Minister’ በሚል ርዕስ ኢትዮጵያ ባለፈው አንድ አመት የሰብአዊ መብት አያያዝ ምን እንደሚመስል ከተለያዩ የሰብአዊ መብት አከባበር መስፈርቶች አንፃር በየዕለቱ ሪፖርቶችን እያወጣ ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ወደ ስልጣን ከመጡ ካለፈው አመት መጋቢት ወር ጀምሮ በሃገሪቱ የታዩ የሰብአዊ መብት አያያዝ ጉዳዮችን አንድ በአንድ በዝርዝር ሪፖርት አስደግፎ እያወጣ የሚገኘው ተቋሙ የመሰብሰብና የመደራጀት ነፃነት (Freedom of Assembly) እንዲሁም ሃሳብን በነፃነት የመግለፅ መብት (Freedom of Expression) በሚሉት ርዕሰ ጉዳዮች ዙሪያ ባካሄደው ያለፈው አንድ አመት ግምገማ ላይ ትኩረት ያደረገ ሪፖርቱን ይፋ አድርጓል።

ከላይ በተጠቀሱት መስፈርቶች አንፃር ያለፉት አመታት በሃገሪቷ የነበረው ሁኔታ እጅግ አፋኝ እንደነበረ ያወሳው ሪፖርቱ ይህ ሁኔታ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ወደ ስልጣን ከመጡ በኋላ ግን መሻሻል እንደታየበት አንስቷል።

እንደ ሪፖርቱ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ ስልጣን በመጡ በአራት ወር ጊዜ ማለትም ሰኔ ወር ላይ ተጥሎ የነበረውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማንሳታቸው በጎ ጅምር ሆኗል። በእሳቸው የመጀመሪያ ሃላፊነት አመት ጥቂት የተቃውሞ እንቅስቃሴዎች ቢኖሩም እንደ ከዚህ ቀደሙ ተመጣጣኝ ያልሆነ ሃይል የመጠቀሙ ሁኔታ እንዳልነበረ የጠቀሰው ሪፖርቱ በአንዳንድ የኦሮሚያ፣ የትግራይና ድሬደዋ አከባቢዎች የክልል ታጣቂ ሃይሎች ተመጣጣኝ ያልሆነ ሃይል የመጠቀሙ ሁኔታ መስተዋሉን ጠቁሟል። በቡራዩ የተከሰተውን ግጭት ተከትሎ በአዲስ አበባ በተከሰተው ተቃውሞ ላይ የፀጥታ ሃይሎች በወሰዱት እርምጃ ቢያንሰ 23 ሰዎች መገደላቸውን በአስረጂነት አንስቷል።

በነፃነት የመሰብሰብና የመደራጀት መብትን አስመልቶም ሪፖርቱ ከዚህ ቀደም እንኳን የሰብአዊ መብቱ ሊከበር ቀርቶ የደረሰውን ጉዳት ለመመርመር እንደማይፈቀድ ገልፆ በአብይ መንግስት ግን ቀሪ ጉዳዮች ቢኖሩም መሻሻል እንዳለ አመልክቷል።

ሪፖርቱ ሃሳብን በነፃነት የመግለፅ መብትን አስመልክቶ ባለፈው ሰኔ ወር ላይ የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ መንግስት መረጃዎች ያለማንም ከልካይ በነፃነት እንዲሰራጩ የሚያስችሉ፤ ተዘግተው የነበሩ የተለያዩ የጡመራ ብሎጎችን እና የዜና ድረገፆችን ጨምሮ 264 ዌብሳይቶች እንዲከፈቱ ማድረጉን አስታውሷል። በአሸባሪነት ተፈርጀው የነበሩት ኢሳት እና ኦ ኤም ኤንን የመሳሰሉ የሚዲያ ተቋማት ክሱ ተነስቶላቸው ያለማንም ክልከላ ተግባራቸውን እየተወጡ ይገኛሉ፤ ብሏል ሪፖርቱ።

በሃገሪቱ እስር ቤቶች ይገኙ የነበሩ ጋዜጠኞች በሙሉ ከእስር እንዲለቀቁ መደረጉን ያተተው ሪፖርቱ ይህም ከፈረንጆቹ 2004 ዓ.ም አንሰቶ የመጀመሪያው እንደሆነም አስቀምጧል። በመንግስት ቁጥጥር ስር የሚገኙ መገናኛ ብዙሃን ራሳቸው ከዚህ ቀደም አይነኬ በሆኑ ጉዳዮች ዙሪያ ዘገባዎቻቸውን እያሰራጩ እንደሚገኙ ያነሳው ሪፖርቱ የተለያዩ የሰብአዊ መብት ጥሰት ዘገባዎችን በየጊዜው እያቀረቡ እንደሆነም አክሏል። ባለፉት አመታት ይፈፀሙ የነበሩ የሰብአዊ መብት አያያዝ ችግሮች ላይ ያተኮሩ ዘጋቢ ፊልሞችን ሲያሰራጩ መታየቱን ሪፖርቱ አካቶ ከዚህ ቀደም በእነዚሁ የመንግስት ሚዲያዎች ይቀርቡ የነበሩ ዘጋቢ ፊልሞች የሰብአዊ መብት ተጠቂውን መብት ለመንፈግ እንደነበርም አመልክቷል።

ይሁን እንጂ እንደ ሪፖርቱ ለአጭር ጊዜም ቢሆን ግጭት በነበረባቸው አካባቢዎች ላይ የኢንተርኔት አገልግሎት እንዲቋረጥ ተደርጎ ነበር። በቅርቡም መንግስት አወጣለሁ ያለውን የጥላቻ ንግግር ህግ ወደ ተግባር በሚቀይርበት ወቅት የመናገር ነፃነትን አደጋ ላይ እንዳይጥለው ሪፖርቱ ስጋቱን አስቀምጧል። በዘገባ ላይ የነበሩ የመረጃ ቲቪ ጋዜጠኞች በክልል የፀጥታ ሃይሎች የማዋከብ አልፎ ተርፎም የእስር እንግልት እንደደረሰባቸውም  አክሏል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከዚህ ቀደም ስራ ላይ ሲውል የነበረውን የመገናኛ ብዙሃን እና የመረጃ ነፃነት አዋጅ እንደገና እንዲታይ ለማድረግ ቃል የገቡ መሆናቸውን የጠቆመው የተቋሙ ሪፖርት ወደ ተግባር የመጣ ነገር እንደሌለም አንስቷል።

ሪፖርቱ በነፃነት ከመሰብሰብ፣የመደራጀት መብትና ሃሳብን በነፃነት ከመግለፅ አንፃር ለወደፊቱ ቢተገበሩ ብሎ ምከረ ሃሳቦችን አስቀምጧል።

የህዝቡን በነፃነት ተሰብስቦ ሰላማዊ ሰልፎችን የማድረግ እና ሃሳቡን የመግለፅ መብቶች ሳይሸራረፉ ማክበር እንዲሁም  የፀጥታ ሃይሎችም ለሚወስዱት ተመጣጣኝ ያልሆነ እርምጃ እንደየ ደረጃቸው ሃላፊነት ሊወስዱ እና መንግስትም በዚህ ረገድ ለፌደራልም ሆነ ለክልል የፀጥታ ሃይሎች ተገቢውን ስልጠና ሊሰጣቸው እንደሚገባ ሪፖርቱ መክሯል። ጠቅላይ ሚኒስትር አብይም ህዝቡ በማንኛውም ጉዳይ ሰላማዊ ተቃውሞ የማሰማት መብት እንዳለው ለህዝቡ ማሳወቅ እንደሚጠበቅባቸውም ሪፖርቱ ጠቁሟል።

መንግስት የሃገሪቱን የሚዲያም ሆነ የኮምፒውተር ወንጀል ህጎችን በማሻሻል ሃሳብን በነፃነት የመግለፅ መብትን ዋስትና እንዲኖረው ሊያደርግ እንደሚገባ ምክረ ሃሳቡን የለገሰው ሪፖርቱ በበይነ መረብ እየተሰራጩ የሚገኙ የጥላቻ ንግግሮችን ለመግታት ተፈፃሚ ለመሆን የሚወጡ ህጎች ሃሳብን በነፃነት የመግለፅ መብትን እንዳይጋፉ ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባም አመልከቷል። ጋዜጠኞች ስራቸውን በነፃነት እንዲያከናውኑ መከታ ሊሆንላቸው የሚችል ህግ ተግባራዊ ማድረግ አስፈላጊ ነው ያለው ሪፖርቱ ከአዲስ አበባ ውጪ ለሚንቀሳቀሱ ነፃ ሚዲያዎች እገዛ ማድረጉ ተገቢ እንደሆነም መክሯል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም