ባለፈው አንድ አመት 306 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ መሰብሰቡን የገቢዎች ሚኒስቴር አስታወቀ

54

አዲስ አበባ መጋቢት 25/2011 የገቢዎች ሚኒስቴር ባለፈው አንድ አመት በተቋሙ የሰው ኃይል እና አሰራር ላይ ባደረገው ለውጥ በመታገዝ 306 ቢሊዮን ብር ገቢ መሰብሰቡን አስታወቀ።

በጉምሩክ መቆጣጠሪያ ኬላዎች ላይ በተደረገው ጥብቅ ቁጥጥር 1 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር ግምት ያላቸው ህገ ወጥ ገቢና ወጪ እቃዎች እንዲሁም የተለያዩ አገሮች የገንዘብ ኖት መያዛቸው ተገልጿል።

የገቢዎች ሚኒስቴርና የጉምሩክ ኮሚሽን ከመጋቢት እስከ መጋቢት በለውጥ ሂደት ባስመዘገቧቸው ስኬቶችና በገጠሙ ተግዳሮቶች ላይ ከተቋማቱ ሰራተኞች ጋር ዛሬ ውይይት ተደርጓል።

በዚሁ ወቅት የገቢዎች ሚኒስትር ወይዘሮ አዳነች አቤቤ እንዳሉት፤ ባለፉት አመታት በገቢዎችና ጉምሩክ ላይ ህብረተሰቡ የሚያነሳቸው በርካታ ቅሬታዎች ነበሩ።

ፍትሀዊ የሆነ የግብር አሰባሰብ አለመኖሩን፣  በቀረጥ ነፃ መብት ተጠቅመው የሚነግዱ በመኖራቸው ተወዳዳሪ መሆን እንዳልቻሉ ተገልጋዮች ሲያነሱ እንደነበር አስታውሰዋል።

ከዚህም በተጨማሪ ተቋሙ ከጉምሩክና ከገቢዎች ጋር ተያይዘው የሚነሱ ችግሮችን ለመቅረፍ ያለውን አደረጃጀትና የሰው ኃይል መልሶ የማደራጀት ስራ ተሰርቷል።

በተጨማሪም ተገልጋይን ያማርሩ የነበሩ አሰራሮችን የማዘመንና ህግና መመሪያዎችንም የመከለስ ስራ መሰራቱን ሚኒስትሯ ገልፀዋል።

የጉምሩክ ስራን ለማቀላጠፍ 55 የነበሩት ኬላዎች ወደ 94 ማደጋቸውን ተናግረው ተገቢ ባልሆኑ ቦታዎች ላይ የነበሩ ኬላዎች ማስተካከያ እንደተደረገባቸውም ጠቁመዋል።

ተቋሙ በህዝብ ዘንድ የታመነ እንዲሆንና ግብርና ታክስን የህዝብ አጀንዳ ለማድረግ የተለያዩ የንቅናቄና ግንዛቤ መድረክ መካሄዳቸውንም ገልፀዋል።

እስካሁን የተሰሩ ስራዎች ካስመዘገቡት ለውጥ በተጨማሪ ለቀጣይ ስራ መደላድል የሚፈጥሩ ተግባራት መሆናቸውንም ተናግረዋል።

ከመጋቢት እስከ መጋቢት በለውጡ የተገኙ ስኬቶችና የገጠሙ ተግዳሮቶች ላይ ውይይት ያደረጉት ከቡድን መሪ እስከ ከፍተኛ አመራር ድረስ ያሉ 1 ሺህ 32 የተቋማቱ ሰራተኞች ናቸው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም