በዓመቱ በዲፕሎማሲው መስክ ውጤታማ ተግባራት ተከናውኗል ተባለ

47

አዲስ አበባ  መጋቢት 25/2011 ባለፈው አንድ ዓመት በዲፕሎማሲው መስክ ውጤታማ ተግባራት መከናወናቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ሂሩት ዘመነ ገለጹ። 

ሚኒስትር ዴኤታዋ ዛሬ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ፤ ባለፈው አንድ ዓመት በአገሪቱ የተካሄዱ የለውጥ ሥራዎች በዲፕሎማሲና በውጭ ግንኙነት ሥራው ላይ አዎንታዊ ሚና ተጫውቷል። 

ከኤርትራ ጋር ከሁለት አስርት ዓመታት በላይ የቆየው አለመግባባት እንዲቋጭና በአፍሪካ ቀንድ የሠላም አየር እንዲነፍስ የተሰራው ስራ ከለውጡ አብነቶች መካከል የሚጠቀስ መሆኑን አስረድተዋል።

ይህም ለሌሎች የአፍሪካ አገሮች ትልቅ ምሳሌ መሆኑንና፤ በሠላም ማስከበር ሥራ ላይም ኢትዮጵያ ያላትን ተደማጭነት ያጠናከረችበት ዓመት እንደነበር ተናግረዋል።    

በውጭ ያሉ የኢትዮጵያ ኤምባሲዎችና ሚሲዮኖች በባህር ማዶ ከሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ጋር ተቀራርበው እንዲሰሩ በማድረግ ወደ አገር ቤት የሚላከው ገንዘብ እንዲጨምር ተደርጓል ብለዋል። 

በተመሳሳይ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትና በሌሎች አማካይነት ወደ አገር የሚገባው የውጭ ፋይናንስ መጨመሩንም ጠቁመዋል።

በዚሁ ዓመት በአፍሪካ ደረጃ ነጻ የንግድ ቀጣና ሥምምነትንም በማጽደቅ በአህጉሪቱ የሚከናወነውን የንግድ ሥርዓት ነጻ ለማድረግ የተጀመረውን ጥረት በመደገፍ አጋርነቷን አሳይታለች ብለዋል።

የዜጎችም መብት ለማስከበር በተሰራው ሥራ በተለይም ከመካከለኛው ምስራቅ አገራት ጋር የውጭ አገራት የሥራ ሥምሪት ሥምምነት መደረሱን ነው የጠቆሙት። 

በአጠቃላይ በዓመቱ የተሳካ የውጭ ግንኙነትና የዲፕሎማሲ ሥራ መሰራቱን ሚኒስትር ዴኤታዋ ጠቁመዋል።

የተገኙትን መልካም ውጤቶች በማስቀጠል በተለይም የተቋሙን የሰው ኃይል እጥረት በመሙላት በቀጣይ የተሳካ ሥራ ለመሥራት ቁርጠኛ መሆናቸውን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም