በትግራይ በቲቢ በሽታ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር እየቀነሰ መምጣቱ ተገለጸ

64

መቀሌ መጋቢት 25/2011 በትግራይ በቲቢ በሽታ የሚያዙ የሰዎች ቁጥር እየቀነሰ መምጣቱን የክልሉ ጤና ቢሮ አስታወቀ።

የበሽታው ስርጭት አሁንም  ትኩረት እንደሚሻ ተገልጿል።

በክልሉ ጤና ቢሮ የበሽታዎች መከላከልና መቆጣጠር የሥራ ሂደት አስተባባሪ አቶ አረጋይ ገብረመድህን ለኢዜአ እንደገለጹት በክልሉ ዘንድሮ ለምርመራ ከቀረቡ 100 ሺህ ሰዎች መካከል 164ቱ የቲቢ በሽታ ተገኝቶባቸዋል።

በዚህም ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወራት ጋር ሲነጻጸር የሕሙማኑ ቁጥር በ43 ወይም በ4 ነጥብ 6 በመቶ መቀነሱን አስረድተዋል።

በክልሉ ከ600 በላይ ጤና ተቋማት የሚሰጠው የቲቢ ምርመራና ሕክምና መሰጠቱ ስርጭቱ ለመቀነስ እንዳስቻለው አስተባባሪው አመልከተዋል።

በተጨማሪም ከ33ሺህ በላይ አባላት ያሏቸው የሴቶች የጤና ልማት ቡድኖች አባላት በበሽታው መተላለፊያና መከላከያ መንገዶች ተከታታይ ትምህርት በመስጠቱ መሆኑንም ተናግረዋል።

በበሽታው ተይዘው ከሚገኙ ሕሙማን መካከልም የጤና ባለሙያዎችን ምክር በመተግበር ወደ ጤናማ ሕይወት የተመለሱት 72 በመቶ እንደሆኑም ገልጸዋል።

ቀሪዎቹ ሕሙማን በክትትልና በመድኃኒት አወሳሰድ ችግር ሳቢያ ከመድኃኒት ተላምደው እንደሚኖሩ አቶ አረጋይ አስረድተዋል።

ቢሆንም የበሽታው ስርጭት መቀነስ የሚያኩራራ ባለመሆኑ ኅብረተሰቡ ጥንቃቄ እንዲያደርጉ አሳስበዋል።

በመቀሌ ሆስፒታል የቲቢ ሕክምና ባለሙያ ዶክተር ማርሊን ፍሥሐ በሕዝቡ ዘንድ በተፈጠረው ግንዛቤ የበሽታው ስርጭት ቅናሽ በማሳየቱ በሆስፒታሉ የነበረው መጨናነቅ ጭምር ቀንሷል ብለዋል።

በበሽታው የተያዙ ሰዎች ለስድስት ወራት የሚታዘዝላቸውን መርፌና ኪኒን በመውሰድ ከበሽታው መፈወስ እንደሚችሉ መክረዋል።

በመቀሌ ሆስፒታል በቲቢ በሽታ የተያዙት አቶ ሰሎሞን ውበት ከአንድ ዓመት በፊት የታዘዘላቸውን መድኃኒት በአግባቡ ባለመውሰዳቸው በሽታውን ተላምደው ለመኖር መገደዳቸውን ገልጸዋል።

''መድኃኒቱን በስድስት ወራት ውስጥ በሚገባ መስጄ መዳን ሲገባኝ ራሴን በፈጠርኩት ቸልተኝነት ምክንያት አሁን በሆስፒታል ውስጥ ሆኜ ለሁለት ዓመታት የሚወስደውን ሌላ መድኃኒት ለመጀመር ተገድጃለሁ’’ ብሏል።

ወጣት ሰለሞን ኃይለማርያም በሆስፒታሉ በግማሽ ዓመት ውስጥ እንዲከታተል የተሰጠውን መድኃኒት ባለመከታተሉ በሆስፒታሉ ለሁለት ዓመታት ተኝቶ በመጠቀም ላይ ነው።

ለበሽታው ዳግም የተጋለጥኩት ለስድስት ወራት እንዲጠቀምበት የተሰጠውን መድኃኒት በአጠቃቀም ጉድለት በማሳየቴ ነው ብሏል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም