የአምስት አፍሪካ አገሮች ኩባንያዎች የጸሀይ ኃይል ለገጠር ነዋሪዎች ማቅረብ የሚችሉበት ውድድር ይፋ ሆነ

59

አዲስ አበባ  መጋቢት 25/2011 ኢትዮጵያን ጨምሮ በአምስት የአፍሪካ አገሮች የሚገኙ ኩባንያዎች የጸሀይ ኃይል (ሶላር) ለገጠር ነዋሪዎች ማቅረብ የሚችሉበት ውድድር ይፋ ሆነ።   

ለሁለተኛ ጊዜ የሚካሄደው ውድድሩ 'የአፍሪካ ኢንተርፕራይዝ ቻሌንጅ ፈንድ' በተሰኘ ተቋም የተዘጋጀ ሲሆን የእንግሊዙ ዓለም አቀፍ ልማት ድርጅት ለመርሀ ግብሩ ማስፈጸሚያ 16 ሚሊዮን ፓውንድ ድጋፍ አድርጓል።                

የውኃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴርን ጨምሮ የተለያዩ ባለድርሻ አካላት በተገኙበት ውድድሩ ዛሬ ይፋ ሆኗል። 

በውድድሩ በኢትዮጵያ፣ ሶማልያ፣ ጋና፣ ናይጄሪያና ሴኔጋል የሚገኙ የግል ኩባንያዎች ለገጠር ነዋሪዎች የተሻለ የጸሀይ ኃይል ቴክኖሎጂን ለማቅረብ ይወዳደራሉ።    

አሸናፊዎቹ ከተመደበው ፈንድ ላይ ከወለድ ነጻ ብድር፣ ተከፋይ ድጋፍ፣ ለግሉ ዘርፍ የሚሰጥ የቴክኒክ ድጋፍና መሰል እገዛዎችን እንደሚያገኙ ነው የተገለጸው።    

በተመጣጣኝ ዋጋ የኃይል ተጠቃሚነትን ማረጋገጥና ተደራሽነትን ማስፋት የውድድሩ ዓላማ እንደሆነም ነው የተጠቆመው።      

የውኃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ፍሬህይወት ወልደሃና በዚሁ ወቅት እንደተናገሩት፤ ኤሌክትሪክን ለማዳረስ እየተሰሩ ያሉ ተግባራት በቂ አይደሉም።

አሁንም በገጠር የሚኖሩ 11 ሚሊዮን ዜጎች የኤሌክትሪክ ተጠቃሚ ሊሆኑ እንዳልቻሉ ገልጸዋል።

ውድድሩ በኃይል አቅርቦት ላይ ለተሰማሩ የግል ኩባንያዎች ሰፊ የገበያ ዕድል መሆኑን ጠቅሰው መንግሥት የሚያበረታታው እንደሆነ ተናግረዋል።

ፈጣን ኢኮኖሚያዊ ሽግግር ለማምጣት አስተማማኝ የኃይል ምርት ሊኖር እንደሚገባ የገለጹት ዶክተር ፍሬህይወት ያለ በቂ የኃይል አቅርቦት ኢንዱስትሪ ማስፋፋት፣ የግብርና እሴት መጨመር፣ ስራ ዕድል ፈጠራና ዘላቂ ኢኮኖሚን ማረጋገጥ አዳጋች እንደሚሆን አስረድተዋል።         

የውድድር ፕሮጀክቶች በኢትዮጵያ የኃይል አቅርቦቱ እንዲሳለጥ አዎንታዊ ሚና እንደሚኖራቸው ተናግረዋል።    

በአፍሪካ ጥቅም ላይ ያለው ታዳሽ ኃይል 18 በመቶ ብቻ መሆኑን የገለጹት ደግሞ የፈንዱ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ዶክተር ዳንኤል ኦሆንዴ፤ ''ታዳሽ ኃይል በአፍሪካ በስፋትና በትኩረት ሊሰራበት ይገባል'' ብለዋል።

ተወዳዳሪ ኩባንያዎች መነሻ ሃሳብ ሲያቀርቡ የሚጠይቁት የገንዘብ መጠን ከ100 ሺህ እስከ 1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ዶላር ድረስ ብቻ መሆኑን በመስፈርቱ ውስጥ ተካቷል። 

በጸሃይ ኃይል አቅርቦት ላይ የሚሳተፉ ድርጅቶች በተመረጡት አገሮች ውስጥ የሚንቀሳቀሱ ኃላፊነታቸው የተወሰኑ የግል ኩባንያ መሆን እንዳለባቸውም ተቀምጧል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም