በበልግ 2 ነጥብ 1 ሚሊዮን ሄክታር መሬት በሰብል ለመሸፈን እየተሰራ ነው

205

አዲስ አበባ  መጋቢት 25/2011 በአገሪቱ በበልግ ወቅት 2 ነጥብ 1 ሚሊዮን ሄክታር መሬት በሰብል ለመሸፈን እየተሰራ መሆኑን የእርሻና የተፈጥሮ ኃብት ሚኒስቴር አስታወቀ።

በዚህም ከ29 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ለመሰብሰብ የታቀደ ሲሆን የአርሶ አደሩን ግንዛቤ የማሳደግና አቅም የማጎልበት ሥራ እየተከናወነ መሆኑ ተገልጿል።

በሚኒስቴሩ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ አለማየሁ ብርሃኑ ለኢዜአ እንደተናገሩት የበልግ ወቅት ከመኸር ቀጥሎ ከፍተኛ የግብርና ምርት የሚሰበሰብበት በመሆኑ ትኩረት ይደረግበታል።  

በዚህ ዓመትም ደረቃማና ቆላማነት በሚያመዝንባቸው አከባቢዎች በተለይም በትግራይ ክልል ደቡባዊ ዞን ሙሉ ሥፍራው ላይ የእርሻ ሥራው እንዲጠናከር እየተሰራ ነው ብለዋል።

በተመሳሳይ በአማራ ክልል፤ ሰሜንና ደቡብ ወሎ፣ ሰሜን ሸዋ ዞኖች እንዲሁም በኦሮሚያ ጉጂ፣ ቦረና፣ ምዕራብ አርሲና ሰሜን ሸዋ ዞኖች ላይ ትኩረት መደረጉን ጠቁመዋል። 

በደቡብ ክልልም በከፋ፣ ቤንቺ ማጂ፣ ሸካ፣ ዳውሮ፣ ደቡብ ኦሞ፣ ሰገን ህዝቦች፣ ወላይታ፣ ጋሞ ጎፋ፣ ሲዳማ፣ ጌዲኦ፣ ኮንታ፣ ባስኬቶ ላይም የበልግ የእርሻ ሥራ እንደሚካሄድ አስረድተዋል።

በድምሩም በዚህ ዓመት በእነዚህ ሥፍራዎች 2 ነጥብ 1 ሚሊዮን ሄክታር መሬት ለመሸፈን የቅድመ ዝግጅት ሥራው መጠናቀቁን ገልጸዋል።

እንደ እርሳቸው ገለጻ “በበልግ እርሻ ሥራ የሚሰበሰበው የሠብል ምርት ከአጠቃላይ አገራዊ ዓመታዊ ምርት 30 በመቶ የሚሆነውን ይሸፍናል” 

አርሶ አደሩም ይህንን የምርት ዘመን በአግባቡ እንዲጠቀም ለማስቻል የብሔራዊ ሚቲዎሮሎጂ ትንበያን መሰረት አድርገው እንዲንቀሳቀሱ ግንዛቤ እየተሰጣቸው ነው ብለዋል።

ውኃ አጠር በሆኑ አካባቢዎች የውሃ እቀባ ሥራዎችን እንዲያካሂዱና ቀላል የውሃ መምጠጫና ሌሎች ቴክኖሎጂዎችንም እንዲጠቀሙም ምክር ተሰጥቷቸዋል ነው ያሉት።

ጎን ለጎንም ቶሎ የሚደርሱ የሰብል አይነቶች እንዲዘሩና ማዳበሪያም በአግባቡ እንዲያገኙ በልማት ጣቢያ ሠራተኞች ድጋፍ እየተደረገላቸው መሆኑን አስረድተዋል።

በዚህም መሰረት በአሁኑ ዓመት የበልግ ወቅት 29 ሚሊዮን ኩንታል ምርት እንደሚጠበቅ ተናግረዋል።

ባለፈው የበልግ ወቅት በሠበል የተሸፈነው 1 ነጥብ 8 ሚሊዮን ሄክታር መሬት ነበር።