ተቃውሞ የበረታባቸው የአልጄሪያው ፕሬዚዳንት ቡተፍሊካ ስልጣን ለቀቁ

71

መጋቢት 25/2011 የአልጄሪያ ፕሬዚዳንት አብደልአዚዝ ቡተፍሊካ ከአንድ ወር በላይ ያስቆጠረውን ህዝባዊ ተቃውሞ ተከትሎ ከስልጣን መልቀቃቸውን የሀገሪቱ መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።

ቡተፍሊካ ከስልጣን መልቀቃቸውን ለሀገሪቱ ህገመንግስታዊ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ማሳወቃቸው ተነግሯል።

ላለፉት 20 ዓመታት በስልጣን ላይ የቆዩት ቡተፍሊካ ለአምስተኛ ጊዜ በምርጫ ለመወዳደር የነበራቸውን እቅድ መሰረዛቸውም ይታወቃል።

የአልጄሪያ ወታደራዊ ኃይል የ82 ዓመቱ አዛውንት ቡተፍሊካ ሀገሪቱን መምራት የማይችሉበት ሁኔታ ላይ ስለሚገኙ ከስልጣን እንዲወርዱ ጫና ሲፈጥር ሰንብቷል።

ላለፉት ስድስት ዓመታት በስትሮክ ህመም እየተሰቃዩ የሚገኙት ፕሬዚዳንት ቡተፍሊካ ስልጣን መልቀቃቸውን ተከትሎ በርካታ አልጄሪያውያን ደስታቸውን እየገለጹ ነው።

ሰልማው ሰዲቅ የተባለ አስተያየት ሰጪ “ከፈጣሪ ፈቃድ ጋር መቶ በመቶ ዴሞክራሲያዊ ሽግግር እናደርጋለን፤ የፕሬዚዳንቱ ስልጣን መልቀቅ በጣም ተገቢ ነው፤ ነባሩ አስተዳደር ሙሉ ለሙሉ እንዲወገድ ነው የምንፈልገው “ ብሏል።

ቡተፍሊካ ከስልጣን ቢወርዱም የሚፈልጉት እስኪሳካ ድረስ ተቃውሟቸውን እንደሚቀጥሉ የተናገሩም አሉ።

በሀገሪቱ ህገመንግስት መሰረት አዲስ ምርጫ እስከሚካሄድ ድረስ የሴኔቱ አፌ-ጉባኤ ጊዜያዊ ርዕሰ መንግሥት ሆኖ ይሰራል።

ምንጭ፦ቢቢሲ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም