መንግስት የህግ የበላይነትን ለማሰከበር እየወሰደ ያለው እርምጃ እንደሚደግፉ በካፋ ዞን ነዋሪዎች ገለጹ

90

ሚዛን መጋቢት 24/2011 መንግስት የህግ የበላይነትን ለማሰከበርና   የዜጎችን ደህንነት ለማስጠበቅ እየወሰደ ያለውን እርምጃ እንደሚደግፉ በካፋ ዞን ነዋሪዎች ገለጹ ፡፡

በደቡብ ምዕራብ ካፋ፣ ሸካና ቤንች ማጂ ዞኖች ያለውን ችግር ለመፍታት ለአንድ ወር የሚቆይ ጊዜያዊ የሠላምና ጸጥታ  ኮሚቴ በቅርቡ ተቋቋሟል፡፡

በኮሚቴው  አስፈላጊነት ዙሪያ  ግንዛቤ ለማስጨበጥ ከካፋ ዞን ነዋሪዎች ጋር ዛሬ በቦንጋ ከተማ ውይይት የተጀመረ ሲሆን የአካባቢውን የጸጥታ መደፍረስ ለመቆጣጠር  መንግስት እያደረገ ያለው እንቅስቃሴ ተገቢ መሆኑን ተሳታፊዎቹ ተናግረዋል፡፡

ከተሳታፊዎች መካከልም ከአዲዮ ወረዳ የመጡት አቶ አጋረጃ ዳዖሙ " አካባቢያችን በታሪኩ የማያውቀው የጸጥታ መደፍረስ ገጥሞታል" ብለዋል።

መንግስት የህግ የበላይነትን ለማስከበርና ችግሩን ለመፍታት ህብረተሰቡን በማሳትፍ እየወሰደ ያለው እርምጃ ተገቢ በመሆኑ እንደሚደግፉት ገልጸዋል።

ሰላም መንግስት ብቻውን በሚያደርገው ጥረት ብቻ እንደማይመጣና ሁሉም የበኩሉን ሊወጣ እንደሚገባ አመልክተው መንግስት መሰል ግጭትና ጉዳት እንዳይደርስ በትኩረት መስራት እንዳለበትም ጠቁመዋል።

"የግጭት ተሳታፊና ተባባሪ አካላትን በማጋለጥ ከመንግስት ጎን መቆም ይገባል " ያሉት  ደግሞ  ከጨና ወረዳ የመጡት አቶ በየነ ዳኪጉቾ ናቸው።

ጥፋተኛ ግለሰቦችን ለህግ አሳልፎ በመስጠት   ተጠያቂ ማድረግና የሚከሰቱ ግጭቶችን በወጣቶች ስም ማሳበብ መቆም እንደሚገባው አመልክተዋል፡፡

ከመፍትሔ ይልቅ ግጭት አባባሽ የመንግስት አመራሮችን መታገስ እንደማያስፈልግ ጠቁመው የግጭትና አለመግባባት ምክንያት የሆኑ ጉዳዮችን መንግስት ቀድሞና ፈጥኖ መፍትሔ እንዲሰጥ የሚደግፉ መሆናቸው ተናግረዋል።

የቦንጋ ከተማ ነዋሪ  ወይዘሮ በላይነሽ ገብረማሪያም " የዜጎችን ሰላምና ደህንነት ማስጠበቅ የመንግስት ቀዳሚ ተግባር መሆን አለበት "ብለዋል።

የጸጥታ ችግሩ እንዲፈታና አካባቢው ወደነበረበት ሰላሙ እንዲመለስም የሚጠበቅባቸውን እንደሚወጡም ገልጸዋል።

የአካባቢውን የጸጥታ መደፍረስ በመቆጣጠር የዜጎችን ደህንነት ለማስጠበቅና የህግ የበላይነት ለማስከበር መንግስት እየወሰደ ያለው እርምጃ  ተገቢ መሆኑን ነዋሪዎቹ ተናግረዋል፡፡

የዞኑ ጸጥታና አስተዳደር መምሪያ ኃላፊ አቶ ንጉሴ ወልደጊዮርጊስ በበኩላቸው የህግ የበላይነትን የማስከበሩ ስራ ህብረተሰቡን ባሳተፈ መልኩ እንደሚከናወን አስታውቀዋል፡፡

" ባለፉት ወራት በዞኑ በተከሰተ የጸጥታ ችግር በሁለቱ ወረዳዎች ጎባና ዴቻ በሰውና ንብረት ላይ ጉዳት ደርሷል "ብለዋል፡፡

ኃላፊው እንዳሉት ችግሩን በዛላቂነት ለመፍታት የጥፋቱ ተሳታፊዎችና ተባባሪ የነበሩ አካላት  የመለየትና ተጠያቂ የማድረግ ስራ ይካሄዳል፡፡

በቀጣይ ቀናትም ውይይቱ እስከቀበሌ ድረስ እንደሚወርድና በየደረጃው የሚገኝ የህብረተሰብ ክፍል ተሳታፊ እንደሚሆን አመልክተዋል፡፡

" በዞኑ የተከሰተው የጸጥታ ችግር በተደራጁ ቡድኖች የተፈጸመ ነው " ያሉት ደግሞ የካፋ ዞን አስተዳዳሪ፣ ጊዜያዊ የሠላምና ጸጥታ  ኮሚቴ  ሰብሳቢ አቶ ማስረሻ በላቸው ናቸው፡፡

በአካባቢው አስተማማኝ ሰላም በማስፈን የተፈናቀሉ ዜጎችን ወደቀደሙ ቀያቸው እንዲመለሱ እንደሚደረግና ዳግም ግጭት እንዳይከሰት ጠንክረው እንደሚሰሩ ተናግረዋል፡፡

ስራው  ከሀገር መከላከያ ሰራዊትና ከሌላው የጸጥታ መዋቅሩ ጋር በጥምረት እንደሚመራ የገለጹት አቶ ማስረሻ የህብረተሰቡ ተሳትፎ ከፍተኛ ሊሆን እንደሚገባም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

ሀገር ሽማግሌዎች ፣ የኃይማኖት አባቶችና ሌሎችም  ነዋሪዎችና  አመራሮች የተሳተፉበት ይሄው ውይይት  ነገም እንደሚቀጥል ታውቋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም