ምክር ቤቱ የጅምላ ጨራሽ መሳሪያዎችን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የሚያስችል አዋጅ አፀደቀ

67

አዲስ አበባ መጋት 24/2011 የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የጅምላ ጨራሽ መሳሪያዎች ብዜትን በገንዘብ መደገፍን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የሚያስችለውን አዋጅ አፀደቀ።

ምክር ቤቱ ዛሬ ባካሄደው መደበኛ ስብሰባው የጅምላ ጨራሽ መሳሪያዎች ብዜትን በገንዘብ መደገፍን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የሚያስችለውን አዋጅ ጨምሮ ሰባት ከተለያዩ አገራት ጋር የተፈረሙ የትብብር ስምምነት ለማጽደቅ የቀረቡ አዋጆችንም መርምሮ አጽድቋል።

ከፀደቁት አዋጆች መካከል የጅምላ ጨራሽ መሳሪያዎች ብዜትን በገንዘብ መደገፍን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የሚያስችለው አዋጅ በምክር ቤቱ 26ኛ መደበኛ ስብሰባ ቀርቦ ለዝርዝር እይታ ለውጭ ግንኙነትና ሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ መጋቢት 3 ቀን 2011 ዓ.ም ተመርቶ ነበር።

ቋሚ ኮሚቴው በረቂቅ አዋጁ ላይ ሰፊ ውይይት በማድረግ እና አንዳንድ ማሻሻያዎችን በማከል ዛሬ ለምክር ቤቱ ለውሳኔ እንዲቀርብ አድርጎ  ምክር ቤቱ በሙሉ ድምጽ አዋጁን አጽድቆታል።

የውጭ ግንኙነትና ሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ተስፋዬ ዳባ፤ በረቂቅ አዋጁ ምርመራ ሂደት የተከወኑ ተግባራት፣ ጭብጦች፣ በአስረጂነት የተገኙ ኃላፊዎች እና በረቂቅ አዋጁ የተደረጉ ማሻሻያዎችን ጨምሮ የውሳኔ ሃሳቦችን ለምክር ቤቱ አባላት አቅርበው አስረድተዋል።

የአዋጁ መውጣት የተባበሩት መንግስታት የፀጥታው ምክር ቤት በ2004 ዓ.ም ባስተላለፈው ውሳኔ አገራት የጅምላ ጨራሽ መሳሪያዎች ብዜትን በገንዘብ መደገፍን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የሚያስችል የህግ ማዕቀፍ እንዲኖራቸው የሚሰጠውን ምክረ ሀሳብ ኢትዮጵያ ተቀብላ መፈፀሟ የዓለም አቀፍ ግዴታዎችን እንድትወጣ የሚያስችል ነውም ብለዋል።

የህጉ መኖር ደግሞ ወደ አገሪቷ የሚተላለፉ ገንዘቦች እና የኢንቨስትመንት ሥራዎች የተቀላጠፉ የሚያደርግና  በጥርጣሬ እንዳይታዩ፣ ባንኮች በማጣራት ጊዜያቸውን እንዳያጠፉ እንዲሁም ኢንቬስተሮችና አገራት ወደ ኢትዮጵያ ገንዘብ ለማንቀሳቀስ እንዲችሉ የሚያበረታታ ነውም ብለዋል አቶ ተስፋዬ።

ህጉ የጅምላ ጨራሽ መሳሪያዎችን በተደራጀና በተቀናጀ መልኩ ለመከላከልና ለመቆጣጠር የሚያስችል መሆኑን የቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢው አቶ ተስፋዬ ተናግረዋል።

የምክር ቤቱ አባላት ከቋሚ ኮሚቴው የቀረበውን የጅምላ ጨራሽ መሳሪያዎች ብዜትን በገንዘብ መደገፍን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የሚያስችል አዋጅ ከመረመሩ በኋላ በሙሉ ድምጽ አጽድቀውታል።

በተመሳሳይ ምክር ቤቱ መንግስት ከሰባት የተለያዩ አገራት ጋር የተፈራረማቸውን የትብብር ስምምነት ለማጽደቅ የቀረቡ አዋጆችን መርምሮ  አጽድቋል።

በዚህ መሰረትም

1 በኢትዮጵያና ህንድ ሪፐብሊክ መንግስት መካከል በኮሙኒኬሽን ኢንፎርሜሽን እና ሚዲያ ዘርፍ የተፈረመ የትብብር ስምምነት

2 በኢትዮጵያና ኮትዲቯር ሪፐብሊክ መንግስት መካከል የዲፕሎማቲክ እና ሰርቪስ ፓስፖርት ለያዙ ሰዎች ቪዛን ለማስቀረት የተፈረመ የትብብር ስምምነት

3 በኢትዮጵያና ቬንዙዌላ ቦሊቫሪያ ሪፐብሊክ መንግስት የባህል ዘርፍ ትብብር ስምምነት

4 በኢትዮጵያና ጋና ሪፐብሊክ መንግስት በኮሙኒኬሽን ኢንፎርሜሽን እና ሚዲያ ዘርፍ የተፈረመ የትብብር ስምምነት

5 የኦዞን ንጣፍን የሚያሳሱ ኬሚካሎችን ለመቆጣጠር በሞንቴሪያል ፕሮቶኮል ላይ የተደረገውን የኪጋሊ ማሻሻያ ስምምነት

6 በኢትዮጵያና በተባበሩት አረብ ኢምሬቶች መካከል የተፈረመ የዲፕሎማቲክ ፓስፖርት ቪዛን ለማስቀረት የተፈረመ የትብብር ስምምነት እንዲሁም 7 በኢትዮጵያና በተባበሩት አረብ ኢምሬቶች መካከል የተፈረመ የኢንቨስትመንት ማስፋፊያና ጥበቃ ስምምነቶች ናቸው ለምክር ቤቱ ቀርበው በሙሉ ድምጽ የጸደቁት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም