የፖሊስ ሰራዊት አባላት በክልሉ የህግ የበላይነት ለማረጋገጥ በቁርጠኝነት መስራት አለባቸው---ኮሚሽነር አለማየሁ እጅጉ

118

አዳማ መጋቢት 24/2011 የፖሊስ ሰራዊት አባላት በክልሉ ዘላቂነት ያለው አስተማማኝ ሰላም ለማስፈንና የህግ የበላይነት ለማረጋገጥ በቁርጠኝነት መስራት እንዳለባቸው የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር አለማየሁ እጅጉ አሳሰቡ።

የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሌጅ  ለ27ኛ ዙር ያሰለጠናቸው  697  የፖሊስ ሠሰራዊት አባላት ዛሬ አስመረቀ።

በምረቃው ስነስርዓት ወቅት ኮሚሽነሩ እንደገለጹት በክልሉ ብሎም በሀገሪቱ በተፈጠረው መሰረታዊ ለውጥ የትጥቅ ትግሉን አማራጭ አድርገው በውጭ ይንቀሳቀሱ የነበሩ የፖለቲካ ፓርቲዎች ወደ ሀገር እንዲመለሱ ተደርጓል።

"ከአስመራ የተመለሱ የኦሮሞ ነፃነት ግንባር ታጋዮች በመንግስት የፀጥታ ዘርፍ ውስጥ ተቀላቅለው እንዲሰሩ ለማድረግ በተቀመጠው አቅጣጫ መሰረት ኮሚሽኑ ኃላፊነቱን እየተወጣ መሆኑን የዛሬው ምርቃት ማሳያ ነው" ብለዋል።

ወደ ሀገር የተመለሱት የግንባሩ ታጋዮች የተሃድሶ ስልጠና ወስደው  በመረጡት የሥራ መስክ እንዲሰማሩ ምርጫ በመስጠት 766 አባላት በፍላጎታቸው ወደ  ፖሊስነት ሙያ እንዲገቡ መደረጉን አስታውቀዋል።

ሰልጣኞቹ በቆይታቸው ያገኙትን ወታደራዊና ሳይንሳዊ እውቀት በመጠቀም በክልሉ ዘላቂነት ያለው አስተማማኝ ሰላምና የህግ የበላይነት ለማረጋገጥ  በቁርጠኝነት መስራት እንዳለባቸው አሳስበዋል።

ህገ መንግስቱን በማክበርና በማስከበር የተጣለባቸው ኃላፊነት በብቃት መወጣት እንደሚጠበቅባቸውም ኮሚሽነር  አለማየሁ አመልክተዋል፡፡

በየደረጃው የሚገኙ አመራሮች አሁን በአዲስ መልክ ወደ ክልሉ ፖሊስ አባላት የተቀላቀለውን ኃይል በአግባቡ በመቀበል ማስተናገድ እንደሚገባቸውም አስገንዝበዋል።

የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሌጅ ዋና ዳይሬክተር ኮማንደር ጌታቸው ኢታና በበኩላቸው ሰልጣኞቹ ለ935 ሰዓታት በፖሊስ ሳይንስ  በቂ የሙያና የክህሎት ስልጠና መውሰዳቸውን ገልጸዋል።

ኮሌጁ  766 የኦነግ ታጋዮችን በመረከብ የፖሊስ ስልጠና ጀምረው ከእነዚህ ውስጥ  በጤና ፣ በስነ ምግባር እና በሌሎችም  ምክንያቶች 69 የሚሆኑት መቀነሳቸውን አስረድተዋል።

ዛሬ ኮሌጁ በ27ኛ ዙር በሙያና ስነ ምግባር ብቁ የሆኑ 697 አባላትን በማስመረቅ ወደ ኦሮሚያ የፀጥታ ኃይል እንዲቀላቀሉ ማድረጉንም አመልክተዋል።

"የፖሊስ ሠራዊት አባላቱ ግዳጃቸውን ህዝባዊ ወገንተኝነትን ተላብሰውና  ተማኝነታቸውን ጠብቆ በገቡት ቃል መሰረት ማገልገል አለባቸው " ያሉት ደግሞ የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ እንዳሻው ጣሰው ናቸው።

ከተመራቂዎቹ መካከል ረዳት ሳጂን አበራ ኦልሂቃ በሰጡት አስተያየት በህዝቦች የጋራ ትግል የመጣው ለውጥ ተከትሎ ትጥቃቸውን በመፍታት ለሰላማዊ ትግል ወደ ሀገር መግባታቸውን ተናግሯል።

" በአሁኑ ወቅት ስንታገልለት የነበረው የፍትህ፣እኩልነትና ዴሞክራሲ ተስፋ በመኖሩ ክልሉን ለማገልገልና አስተማማኝ ሰላም እንዲሰፍን ባገኘሁት እውቀትና ክህሎት በቁርጠኝነት እሰራለሁ"  ብለዋል።

ተመራቂ የፖሊስ ሰራዊት አባላቱ በስልጠና ላይ የቆዩት ላለፉት  አምስት ወራት መሆኑ ታውቋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም