ምቹ የእግረኛና ሞተር አልባ ተሽከርካሪዎች መንገድ እየገነባሁ ነው-የአ /አ መንገድና ትራንስፖርት ቢሮ

63

አዲስ አበባ መጋቢት 24/2011 የእግረኛና ሞተር አልባ ተሽከርካሪዎችን ማስተናገድ የሚችል ምቹ መንገድ እየሰራ እንደሆነ የአዲስ አበባ መንገድና ትራንስፖርት ቢሮ ገለጸ።

ህብረተሰቡ ሞተር አልባ የትራንስፖርት አገልግሎትን አዘውትሮ እንዲጠቀም የሚያስችለውን ተግባር በማከናወን ላይ መሆኑንም ቢሮው አስታውቋል።

እ.ኤ.አ ከ2019 እስከ 2028 ባሉት አስር ዓመት ውስጥ ከሞተር ነጻ የሆነ ምቹ የትራንስፖርት አገልግሎት ያላት ከተማ ይገነባልም ተብሏል። 

በከተማዋ የእግረኞች ቁጥር 54 በመቶ ያህል ሲሆን 31 በመቶው የህዝብ ትራንስፖርት ተጠቃሚ ነው ።

15 በመቶ ያህሉ ብቻ የግል ተሽከርካሪ ባለቤት ቢሆንም የአገሪቷ የመንገድ ፍሰት ካለው ህዝብና ተሽከርካሪ ጋር እንደማይመጣጠን የተደረገው ጥናት አሳይቷል።

በዚህም ለእግረኞች ምቹ መንገድ በመስራት ከቦታ ቦታ እንዲንቀሳቀሱ የሚችሉበትን አግባብ ለመፍጠር እየሰሩ እንደሆነ የከተማው ምክትል ከንቲባና የመንገድና ትራንስፖርት ቢሮ ሃላፊ ዶክተር ሰለሞን ኪዳኔ ተናግረዋል።

ከእለት ወደ እለት እየተባባሰ የመጣውን የትራፊክ አደጋ ችግር ለመፍታትም ሆነ የአየር ብክለትን ለመከላከል ከሞተር ነጻ የሆኑ የትራንስፖርት አማራጭ መጠቀም ፋይዳው የላቀ ነው ተብሏል።

በእግረኛ መንገዶች ላይ ለግንባታ የሚውሉ ቁሳቁሶች ማከማቸትና ህገ ወጥ ንግድ ማከናወን በመንገዶች ላይ እያደረሱት ያሉት ጉዳትም ሰፊ መሆኑን ጠቁመዋል።

ከዚህ ባለፈ ለትራፊክ አደጋ መፈጠርም ምክንያት ከመሆን ባለፈ እግረኞች የእግረኛ መንገዶችን እንዳይጠቀሙ እያደረጓቸው እንደሚገኙም ገልጸዋል።

በመሆኑም አሁን በተያዘው ስትራቴጅ እነዚህን ችግሮች በመፍታት ምቹና ተመራጭ የሆነ የእግረኞች መንገድ ለማስፋት ታስቧል።

ሰው በሚበዛባቸው ቦታዎች ላይ የትራንስፖርት ችግር ሲያጋጥም አማራጮችን በማስቀመጥ እየሰሩ እንደሆነና ህብረተሰቡ የእግር ጉዞ ሊያደርግባቸው የሚችላቸው ምቹ የእግረኛ መንገዶችን መዘርጋት መጀመራቸውንም አስታውቀዋል።

በዚህም ሁሉንም አካባቢዎች ለማዳረስ  እንደሚሰሩ ነው ዶክተር ሰለሞን የሚገልጹት።

ተቋሙ 10 ሺ የሚጠጉ በኤሊክትሪክ የሚሰሩ ብስክሌቶች በማስገባት እና በተመጣጣኝ ዋጋ ለህብረተሰቡ በኪራይ አገልግሎት እንዲሰጡ ለማድረግ መዘጋጀቱንና የተጠቃሚዎችን ፍላጎት በመመልከትም አቅርቦቱን ለማሳደግ መዘጋጀቱንም ገልጿል።

ከዚህ በተጨማሪም በቂ የሆነ የመኪና ማቆሚያ በከተማዋ ባለመኖሩ በርካታ መንገዶች የመኪና ማቆሚያ ስፍራ በመሆን በማገልገል ላይ ይገኛሉ።

ቢሮው በተደጋጋሚ የትራፊክ አደጋ የሚደርስባቸውን ስፍራዎች በመለየት የፍጥነት ማብረጃ አለማድረጉ አደጋውን እንደጨመረውና ይህንኑ ችግር ለመፍታት በስፋት ለመስራት መዘጋጀቱን ገልጸዋል።

በርካታ የህዝብ ቁጥር ያሏትና  የተሳለጠ የትራንስፖርት አገልግሎት ከሚሰጡ አገሮች አንዷ ቻይና ስትሆን በርካታ ዜጎቿ ሞተር አልባ የትራንስፖርት አገልግሎት ተጠቃሚ ናቸው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም