በሆሳዕና ከተማና አካባቢዋ የኤሌክትሪክ አቅርቦት ወደ 122 ሜጋ ዋት አደገ

51

ሆሳዕና መጋቢት 24 / 2011  በሆሳዕና ከተማና አካባቢዋ የኤሌክትሪክ አቅርቦት ወደ 122 ሜጋ ዋት ማሳደጉን በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የደቡብ ሪጅን አስታወቀ፡፡

አቅርቦቱ ኅብረተሰቡ ያቀርበው የኃይል ጥያቄ ከመመለሱም በላይ፤የከተማዋን የኃይል አማራጮች እንዳሰፋውም ተገልጿል።

በሪጅኑ የኃይል ስርጭት ክፍል ዳይሬክተር አቶ ዓለማየሁ ዘበርጋ ትናንት እንደተናገሩት አቅርቦቱ የአካባቢውን የኃይል አቅርቦት በሁለት እጥፍ አሳድጎታል።

እስከ 20 ዓመት ለሚደርስ ጊዜ  አስተማማኝ አገልግሎት ይሰጣል ብለዋል።

በዚህም ከፍተኛ ኃይል ለሚጠቀሙ ኢንዱስትሪዎችን ለማንቀሳቀስ እንደሚያስችል ገልጸዋል፡፡

አካባቢው አገልግሎቱን የሚያገኝባቸውን አማራጮች በማስፋት ከሐላባና ወልቂጤ ማሰራጫ መሥመሮች ጋር እንደተገናኘም ዳይሬክተሩ ተናግረዋል።

የሐዲያ ዞን ምክትል አስተዳዳሪና የትምህርት መምሪያ ኃላፊ አቶ ሀብታሙ ታረቀኝ በበኩላቸው የአገልግሎቱ ማደግ የኅብረተሰቡን ጥያቄ ከመመለሱም በላይ ባለሀብቶች በኢንዱስትሪና በሌሎች ኢንቨስትመንት መስኮች ለመሰማራት እንደሚያስችላቸው አመልክተዋል፡፡

በከተማዋ በተደጋጋሚ በሚቆራረጠው የኤሌክትሪክ አገልግሎት በብረታ ብረት ሙያ ተሰማርተው ለመስራት ችግር ሆኖባቸው እንደቆየ የተናገረው የሴች ዱና ቀበሌ ነዋሪ ወጣት ብርሃኑ ወልዴ ነው፡፡

ለከተማዋና አካባቢው አቅርቦቱ ማደጉ በብድር የወሰደውን ገንዘብ ለታለመለት ዓላማ ማዋል ያስችለኛል ብሎ እንደሚያምን ተናግሯል፡፡

የሜል አንባ ቀበሌ ነዋሪዋ ወይዘሮ እታፈራሁ ካሳዬ አቅርቦቱ ለእንግልትና ላልተገባ ወጪ ሲዳርጋቸው የነበረውን የኃይል አቅርቦት እንደሚያሻሽለው እምነታቸውን ገልጸዋል።

በሆሳዕና ከተማና አካባቢዋ የኤሌክትሪክ አቅርቦት 56 ሜጋ ዋት ነበር።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም