ሚዲያዎች አሁንም ከፖለቲካ ተፅእኖ ነፃ አይደሉም ተባለ፡-የዘርፉ ባለሙያዎች

79

መጋቢት 24/2011 የሀገሪቱ ሚዲያዎች ለውጡ ያመጣላቸውን እድል ለበጎ ተግባር ከመጠቀም ይልቅ አሁንም ከፖለቲካ ተፅእኖ ነፃ ሆነው እየሰሩ እንዳልሆነ ነው የዘርፉ ባለሙያዎች ተናገሩ።

አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የመገናኛ ብዙሃን ሃላፊዎችና ባለሙያዎች ሚዲያዎች የመንግስትን ጠንካራ ጎን ከመዘገብ ባሻገር ደካማ ጎኖችንም መተቸት እንደሚገባቸው ይገልጻሉ።

ከለውጡ በፊት በአሸባሪነት ተፈርጀው ወደ አገር ውስጥ እንዳይገቡ ተከልክለው ከነበሩ ሚዲያዎች ኢሳት አንዱ መሆኑን የሚናገሩት በኢትዮጵያ የኢሳት ስራ አስኪያጅ ኢንጅነር ሳባ ታሮ ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ ከ8 ወራት በፊት ወደ ሀገር ውስጥ ገብተው እንዲሰሩ በቀረበላቸው ጥሪ መሠረት ሥራ መጀመራቸውን ተናግረዋል፡፡

ከህዝብ ጋር ተገናኝተው መስራት መቻላቸው ትልቅ ለውጥ እንደሆነ የገለጹት ኢንጅነር ሳባ፤ በሀገሪቱ ተዘዋውሮ በነፃነት መስራት የሚቻልበት ምህዳር አለመኖሩን ግን ያነሳሉ።

በሀገራዊ ለውጡ የታሰሩ ጋዜጠኞች መፈታታቸውና የሚዲያ ህጎች መሻሻል መጀመራቸው በጥንካሬ ያነሱት የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የጋዜጠኝነትና ኮሙዩኒኬሽን መምህር አቶ ዳግም አፈወርቅ፤ አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ ግን  ሚዲያዎች ሙሉ በሙሉ ነፃ ናቸው ማለት አይቻልም ይላሉ።

ሚዲያው በሙሉ ነፃነት ሃላፊነት ወስዶ መስራት መቻሉ በሕብረተሰቡ ዘንድ የተሻለ ታማኝነት እንዲያገኝ አድርጓል ያሉት ደግሞ  የዋልታ ሚዲያና ኮሙኒኬሽን ኮርፖሬት ዋና ስራ አስፈፃሚ  አቶ ተተካ በቀለ ናቸው፡፡

ሃሳብን በነፃነት የመግለፅ መብት በህግም ሆነ በሞራል የራሱ የሆነ ገደብ እንዳለው የጠቀሱት አቶ ተተካ አንዳንድ ሚዲያዎች ያገኙትን ነፃነት በአግባቡ ያለመጠቀም ሁኔታ ይታይባቸዋል ይላሉ።

የአሃዱ ሬድዮ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ጥበቡ በለጠ በበኩላቸው ኢትዮጵያ ከአንድ ዓመት ወዲህ ከመቼውም ጊዜ በላይ በሚዲያ ነፃነት ውስጥ መግባቷን በማንሳት “ ይህ ለኔ ታሪካዊ ክስተት ነው ” ብለዋል፡፡

ሆኖም አንዳንድ ሚዲያዎች ቋንቋና ዘራቸውን ማእከል አድርገው የተቋቋሙና የሚሰሩ ናቸው በማለት ስጋታቸውን አንስተዋል።

ዘረኝነት የሚዲያ አሰራር ችግር እየሆነ መምጣቱን ያነሱት አቶ ጥበቡ፤ ሚዲያዎቹ የሚያቀርቧቸው ምሁራን ዘርንና ቋንቋን መሰረት ያደረጉ መሆኑ የመረጃ መዛባትን ሊፈጥር እንደሚችል ነው የተናገሩት፡፡

“ሚዲያዎች በነፃነት ተንቀሳቅሰው እንዲሰሩ በተነገረበት ማግስት መረጃ ለመሰብሰብ ወደ ተለያየ ቦታ የተላኩ ጋዜጠኞች ሲደበደቡ፣ ታግተው ችግር ሲደርስባቸው ምንም ዓይነት እርምጃ አለመወሰዱ በሃገራችን የሚዲያ ነፃነት አለ ብሎ ለመናገር አያስደፍርም” ይላሉ  መምህር ዳግም።

ቀደም ብሎ እንደችግር ሲነሳ የነበረው ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች ለጋዜጠኞች ቢሮአቸውን ዝግ ማድረጋቸው አሁንም አለመሻሻሉን አንስተዋል።

በማስረጃነት የሚያነሱትም በብዙ ሚዲያዎች “የሚመለከተውን አካል ለማግኘት ያደረግነው ተደጋጋሚ ጥረት አልተሳካም” የሚሉ ዘገባዎች በተደጋጋሚ እየተደመጡ መሆናቸውን ነው።

የዋልታ ስራ አስፈጻሚ በበኩላቸው ከለውጡ ወዲህ በሚዲያው ዘርፍ እያጋጠሙ ካሉ ችግሮች መካከል የጋዜጠኝነት ሙያና አክቲቪስትነትን መቀላቀል  በስፋት እንደሚታይ ጠቅሰዋል፡፡

 “ጋዜጠኞች እንደ ሰው ነፃ ናቸው ልንል ብንችልም ከህዝብ በተውሶ የተወሰደው ሚዲያ ላይ የግል የሆነ ሃሳብ ማንፀባረቅ ግን በሚዛናዊነቱ ላይ ጥቁር ጥላሸት መቀባት ነው” ብለዋል፡፡

የክልል ሚዲያዎች ለረጅም ጊዜ ተፈቃቅደውና ተቻችለው በኖሩ ህዝቦች መካከል ጥላቻን ከመንዛት ይልቅ የቆየውን ተቻችሎ በፍቅር አብሮ የመኖር ባህላቸውን ወደ ላቀ ደረጃ በሚያሸጋግር መንገድ እንዲሰሩም ጠይቀዋል፡፡

የሚድያ ነፃነት ሲባል ግን የሀገር አንድነትና የህዝቦችን መብት ታሳቢ ለማያደርግ ለአንድ ሚድያ ተቋም ወይም ጋዜጠኛ የተሰጠ ልቅ ነፃነት ማለት እንዳልሆነ ያነሱት አቶ ዳግም ከሙያው ስነ-ምግባር ውጭ የሆነ አሰራር መከተል የሚዲያውን ተአማኒነት ጥያቄ ውስጥ እንደሚያስገባም ጠቁመዋል።

ሚዲያ በነጻነት ሰራ የሚባለው የፖለቲካና የኢኮኖሚ ተፅእኖ ሳያርፍበት፤ በበቂ እውቀት የተደገፈ ጊዜውንና ሚዛኑን የጠበቀ መረጃ ለማህበረሰቡ ሲያደርስ መሆኑንም አብራርተዋል፡፡

ኢንጅነር ሳባ በበኩላቸው፤ የሀገሪቱ ትልልቅ መድረኮች ላይ ኢሳት እንዲዘግብ የማይጋበዝበት አጋጣሚ መኖሩን በማንሳት ”በሂደት እየተሻሻለ እንደሚሄድ እንጠብቃለን” ነው ያሉት፡፡

የዋልታ ስራ አስፈጻሚ አቶ ተተካ እንዳሉት የተገኘውን ነፃነት ተከትሎ ሚዲያዎች ሙያው በሚፈቅደው መሰረት ራሳቸውን የሚገሩበት አሰራር መዘርጋት አለባቸው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም