ዩኒቨርሲቲዎች ወደ ኢንዱስትሪ መር ኢኮኖሚ ለመሸጋገር የሚደረገውን ጥረት ሊያግዙ እንደሚገባ ተጠቆመ

347

አርባምንጭ መጋቢት 24/2011 ዩኒቨርሲቲዎችከኢንዱስትሪዎች ጋር ተቀራርበው በመስራት ሀገሪቱን ወደኢንዱስትሪ መር ኢኮኖሚ ለማሸጋገር የሚደረገውን ጥረት ሊያፋጥኑ እንደሚገባ ተጠቆመ።

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የፕሮዳክሽን ምህንድስና ተማሪዎችን ከተለያዩ ኢንዱስትሪዎች ጋር ለማገናኘት ያዘጋጀው መድረክ ተካሂዷል።

የዩኒቨርሲቲውፕሬዚዳንት ዶክተር ዳምጠው ዳርዛ በእዚህ ወቅት እንዳሉት ኢትዮጵያን መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገሮች ተርታ ለማሰለፍ የኢንዱስትሪው ሚና የጎላ በመሆኑ በመንግስት ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ነው፡፡

አገሪቱን ወደ ኢንዱስትሪ መር ኢኮኖሚ ለማሸጋገር የሚደረገው ጥረት እንዲፋጠን ዩኒቨርሲቲዎች ከኢንዱስትሪዎች ጋር በቅርበት መስራት እንዳለባቸውም ጠቁመዋል።

ለኢንዱስትሪው የተማረ የሰው ኃይል በማፍራት በኩል አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የበኩሉን እየተወጣ መሆኑን ጠቁመው ለእዚህም በዘርፉ ቀጥተኛ ግንኙነት ያለውን የትምህርት ፕሮግራም ቀርጾ እየሠራ መሆኑን በማሳያነት ጠቅሰዋል፡፡

በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ በተቀረጸውና “ፕሮዳክሽን ምህንድስና” በተሰኘው የትምህርት ዘርፍ ዩኒቨርሲቲው 47 ተማሪዎችን ዘንድሮ የሚያስመርቅ ሲሆን ይህም ወደኢንዱስትሪ መር ለሚደረገው ሽግግር ጠቀሜታ እንዳለው አመልክተዋል።

ኢንዱስትሪዎች ውጤታማ የሚሆኑት በዘርፉ በሰለጠኑ ባለሙያዎች ሲታገዙ ቢሆንም ከከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ጋር ያላቸው ግንኙነት ዝቅተኛ መሆኑን የጠቆሙት ደግሞ በዩኒቨርሲቲ የመካኒካልና ፕሮዳክሽን ምህንድስና ትምህርት ክፍል ዲን አቶ አትክልት ሙሉ ናቸው ፡፡

ይህ ደግሞ በኢንዱስትሪው ዘርፍ ያሉ ማነቆዎችን በጥናትና ምርምር ለመደገፍ እንቅፋት ሆኖ መቆየቱን ነው የገለጹት፡፡

” በአገሪቱ የኢንዱስትሪ አብዮት እንዲፋጠን ዩኒቨርሲቲዎችና ኢንዱስትሪዎች ተቀራርበው ከመስራት ውጪ አማራጭ የለም ” ያሉት አቶ አትክለት ለእዚህም የጋራ ስምምነት ሰነድ አዘጋጅቶ መስራት እንደሚገባ አመልክተዋል።

ከኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን የመጡት ዶክተር ጥላሁን ገመቹ በበኩላቸው የኢንዱስትሪ ልማቱን ለማፋጠን በኢትዮጵያ የተጀመረው የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት እንቅስቃሴ የተሻለ ደረጃ ላይ መሆኑ ገልጸዋል ፡፡

ይህም ለሥራ ዕድል ፈጠራና ለኢኮኖሚ ግንባታ ትልቅ ድርሻ እንዳለው ነው የተናገሩት፡፡

ኢንዱስትሪው በዕውቀት እንዲመራ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ከኢንዱስትሪዎች ጋር ተቀራርበው  መስራት እንዳለባቸውም መክረዋል።

“አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ በፕሮዳክሽን ምህንድስና ትምህርት በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ ባለሙያ ማፍራት መጀመሩ ለኢንዱስትሪው ልማት መፋጠን የጎላ ሚና ስላለው ሊበረታታ ይገባል” ብለዋል ፡፡

“ለአምስት ዓመታት ከዩኒቨርሲቲው ባገኘሁት ዕውቀት በቀጣይ በኢንዱስትሪ ልማት ዘርፍ የበኩሌን ለመወጣት ተዘጋጅቺያለሁ” ያለው ደግሞ በፕሮዳክሽን ምህንድስና ተመራቂ ተማሪ የሆነው ፊልሞን አማሬ ነው ፡፡

ዩኒቨርሲቲዎች ከኢንዱስትሪዎች ጋር ያላቸው ግንኙነት ከተጠናከረ ዘርፉን ተወዳዳሪና ምርታማ ለማድረግ እንደሚያግዝ አስረድቷል ፡፡

በመድረኩ በኢትዮጵያ የሚገኙ የኢንዱስትሪ ፓርኮችን ጨምሮ በርካታ ካምፓኒዎች ተሳትፈዋል ።