በአማራ ክልል የተፈናቀሉ ወገኖችን መልሶ ለማቋቋም የገቢ ማሰባሰቢያ መርሃ ግብር በጋምቤላ ተጀመረ፡፡

54

ጋምቤላ መጋቢት 24/2011የጋምቤላ ክልል በአማራ ክልል ተፈናቃዮችን መልሶ ለማቋቋም የገቢ ማሰባሰቢያ መርሐ ግብር ትናንት ተጀመረ፡፡

በጋምቤላ ከተማ  በተጀመረው መርሐ ግብር ትናንት ከግማሽ ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ ተሰብስቧል።

የጋምቤላ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኡሞድ ኡጀሉ በመርሃ ግብሩ ማስጀመሪያ  ላይ እንደተናገሩት የክልሉ ሕዝብ በአማራ ክልል የተፈናቀሉ ወገኖችን ለመርዳት ሚናውን ሊጫወት ይገባል።

የአማራ ክልል ሕዝብ ችግር የጋምቤላ ብሎም የኢትዮጵያ ችግር መሆኑን በመረዳት የክልሉ ሕዝብ በተለይም ባለሃብቶች ድጋፋቸውን እንዲያደርጉ  ጠይቀዋል።

የክልሉ መንግሥት በመርሐ ግብሩ ስኬታማነት ድጋፍ እንደሚያደርግም ርዕሰ መስተዳድሩ አስታውቀዋል።

ከአማራ ክልል ውጪ የገቢ አሰባሳቢ ኮሚቴ አባል አቶ ፍሥሐ ወልደሰንበት በበኩላቸው በክልሉና ከክልል ውጪ በተፈጠረ ግጭት ከ90 ሺህ በላይ ሕዝብ መፈናቀሉን ተናግረዋል።

በመሆኑም ተፈናቃዮችን በዘላቂነት ለማቋቋም መርሐ ግብር ተቀይሶ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

በክልሉ የተጀመረው የገቢ ማሰባሰቢያ መርሐ ግብር የታየው የሕዝብ ተሳትፎ ''የአንዱ ጉዳት ለሌላውን እንደሚሰማው መሆኑን ያስመሰከረ ነው'' ብለዋል።

በመርሐ ግብሩ ድጋፍ ካደረጉት ባለሃብቶችና ነዋሪዎች መካከል ወይዘሮ አምሳለ ገብረወልድ በሰጡት አስተያየት በግጭቶች ሳቢያ በአማራ ክልል የተፈናቀሉ ወገኖች በተለይም በእናቶችና በህፃናት ላይ የሚደርሰው ጉዳት ለመታደግ ድጋፍ ማድረግ እንደሚያስፈልግ አመልክተዋል።

''የኢትዮጵያ ሕዝብ በአንድነት ተቻችሎ የመኖር ትልቅ እሴት ያለው ሕዝብ ነው'' ያሉት ሌላዋ አስተያየት ሰጪ ወይዘሮ መብራት ብስራት፣ ሕዝቡን ለመፈናቀል እየዳረጉ ያሉትን ግጭቶች  ለማስቆም መስራት ያስፈልጋል ብለዋል።

ሌላው የመርሐ ግብሩ ተሳታፊ አቶ ኡጆም ኡጁሉ በሰጡት አስተያየት በመርሐ ግብሩ በአማራ ክልል ተፈናቃዮች ድጋፍ ለማድረግ መገኘታቸውን ተናግረዋል፡፡

እስከ ሚያዝያ 10/2011 በሚቆየው መርሐ ግብር በሁሉም የክልሉ ዞኖችና ወረዳዎች ይካሄዳል፡፡ 

የክልሉ መንግሥት በአገር አቀፍ ደረጃ በአዲስ አበባ በተካሄደው የገቢ ማሰባሰቢያ ቴሌቶን ላይ የሶስት ሚሊዮን ብር ድጋፍ አድርጓል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም