በባህርዳር ከተማ የተቋቋሙ የወጣት ማዕከላት ተገቢውን አገልግሎት እየሰጡ አይደለም ተባለ

123
ባህር ዳር ግንቦት 24/2010 በባህርዳር ከተማ የተቋቋሙ የወጣት ማዕከላት በገጠማቸው የፋይናንስ እጥረት ምክንያት ተገቢውን አገልግሎት እየሰጡ እንዳልሆነ አመራሮቹ ገለፁ። የማዕከላቱ አመራሮች ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንደገለጹት ወጣቱ ትውልድ የእረፍት ጊዜውን አለባሌ ቦታ እንዳያሳልፍና አካላዊና አዕምሮአዊ ብቃቱን ለማጎልበት የተቋቋሙት እነዚህ ማዕከላት የገንዘብ እጥረት ገጥሟቸዋል። የወጣት ማዕከላት ሰፋፊ የመስሪያ ቦታ ተሰጥቷቸው የተቋቋሙ ቢሆንም በፋይናንስ እጥረት ምክንያት አስፈላጊ ግብአቶችን አሟልቶ አገልግሎት ለመስጠት መቸገራቸውን የየማዕከሉ አመራሮች ተናግረዋል። የሰፈነ ሰላም ክፍለ ከተማ ወጣቶች ማዕከል ስራ አስኪያጅ ተወካይ ወጣት ጌትነት መኩየ እንደገለጸው ለማዕከል  የሚሆን ቦታ በነጻ ከመስጠት ውጪ መንግስት ምንም አይነት ክትትልና ድጋፍ እያደረገ አይደለም። ቦታ መስጠቱ ብቻ ውጤት እንደማያስገኝ የገለጸው ወጣት ጌትነት ''ማዕከላቱ የታለመላቸውን አላማ እንዲያሳኩ በመጠኑም ቢሆን መደጎሚያ በጀት በመመደብ መንግስት የወጣቱን ፍላጎት የሚያሟሉ ግብዓት ሊያቀርብ ይገባል'' ብሏል። “በማዕከላቱ የስፖርት ማዘውተሪያዎችና የዕውቀት ማበልጸጊያ ቁሳቁሶች ማጠናከር ግድ ይላል'' ያሉት አመራሮቹ  እንደ መረብ ኳስ፣ ቅርጫት ኳስ ፣ ጠረጼዛ ቴነስ፣ ቤተ-መጽሃፍትና የኢንተርኔት አገልግሎት በተጨማሪም የህይወት ክህልት ስልጠና እንዲያገኙ ታስቦ የተቋቋሙ መሆናቸውን አስታውሰዋል። ነገር ግን ማዕከላቱ በፋይናንስ እጥረት ምክንያት  የሚገባቸውን አገልግሎቶች እየሰጡ እንዳልሆነ ገልጿል፡፡ ወጣት ጌትነት እንደሚለው የወጣት ማዕከላት ተገቢው ትኩረት ቢሰጣቸው  የወጣቱን ማህበራዊ አንድነት ለማጠናከርም ከፍተኛ አስተዋጽኦ ይኖረዋል። የሽምብጥ ክፍለ ከተማ ወጣቶች ማዕከል ስራ አስኪያጅ ወጣት ታየ አስፋው በበኩሉ ''ለወጣት ማዕከላት የሚደረገው ክትትልና ድጋፍ  ውሱን ነው'' ብሏል። ''እንደ ወጣት ታየ ገለጻ መንግስት ወጣት ማዕከላትን በየቦታው ገንብቶ ከማስረከብ ውጭ ያሉበት ሁኔታ ምን እንደሚመስልና  የሚያስፈልጋቸውን ድጋፍ ከማሟላት አኳያ ከፍተኛ ውስንነት አለበት፤ይህ በመሆኑም ማዕከላቱ ለታለመላቸው አላማ እየዋሉ አይደለም'' ሲል ገልጿል። የክልሉ ባህል፣ ቱሪዝም፣ ወጣትና ስፖርት መምሪያ ምክትል ኃላፊ አቶ አብረሃም አሰፋ እንደገለጹት ማዕከላቱ ከመብዛታቸው የተነሳ አጥጋቢ ክትትልና ድጋፍ እየተደረገ አለመሆኑን አምነዋል፡፡ በመሆኑም በአሁኑ ወቅት የወጣት ማዕከላትን የሚከታተል  ባለሙያ ተመድቦ እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡ ይሁን እንጂ መንግስት ሙሉ ለሙሉ እየደገፈ አይደለም በሚለው አስተያየት አይስማሙም። የወጣት ማእከላት ሲቋቋሙም የራሳቸውን ገቢ በማመንጨት እንዲተዳደሩ  መሆኑን የገለጹት አቶ አብረሃም ማዕከላቱ የተሰጣቸውን ምቹ የመስሪያ ቦታ ወደ ቢዘነስ በመቀየር ገቢ ሊያመነጩበት እንደሚገባም አስገንዝበዋል። በማዕከላቱ የሚታዩ  የቁሳቁስ እጥረቶችን ለመፍታት መንግስት ከባለድርሻ አካላት ጋር እየሰራ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡ በባህርዳር ከተማ አስተዳደር  ሰባት የወጣት ማዕከላት እንደሚገኙ ከመምሪያው የተገኘ መረጃ ያስረዳል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም