የባሌ ዞን ዓመታዊ የስፖርት ሻምፒዮና ውድድር ተጀመረ

268

ጎባ መጋቢት 23/2011 የባሌ ዞን ዓመታዊ የወረዳዎች የስፖርት ሻምፒዮና ውድድር ዛሬ በጎባ ስቴዲዮም ተጀመረ ።

የዞኑ ስፖርት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሰለሞን ተክሌ በመክፈቻው ስነስርዓት ወቅት እንደገለጹት የውድድሩ ዓላማ በቅርቡ በነቀምቴ በሚካሄደው የመላው ኦሮሚያ ጨዋታዎች ላይ የባሌ ዞንን ወክለው የሚሳተፉ ስፖርተኞችን ለመምረጥ ነው፡፡

“በስፖርት የዳበራና በሀገር ልማት ውስጥ ንቁ ተሳትፎ የሚያደርግ ጤናማ ወጣት መፍራት ሌላው የውድድሩ ዓላማ ነው “ብለዋል፡፡

በውድድሩ ከሚካሄዱት መካከል  እግር ኳስ፣ ቦሊቦልና አትሌትክስ ይገኙበታል፡፡

የዞኑ ዋና አስተዳዳሪና የስፖርት ምክር ቤት ሰብሳቢ አቶ ኢብራሂም ሀጂ በበኩላቸው  ተሳታፊዎቹ በስፖርታዊ ጨዋነትና በመቻቻል ውድድራቸውን እንዲያካሂዱ አሳስበዋል፡፡

ወጣቶች በሀገሪቱ የተጀመሩ ሁሉን አቀፍ ለውጦች ከዳር እንዲደረሱ በግንባር ቀደምትነት እንዲደግፉም  መልዕክታቸውን አስተላልፏል፡፡ 

በመክፈቻው ወቅት  በተካሄደ የእግር ኳስ ውድድር የጎባ ከተማ የስፖርት ቡድን የጊኒር ወረዳ አቻውን ሶስት ለሁለት  በሆነ ውጤት አሸንፏል፡፡

ለአንድ ሳምንት በሚቆየው ውድድር ከ18 ወረዳዎች የተውጣጡ አንድ ሺህ የሚጠጉ ስፖርተኞች እንደሚሳተፉ ተገልጿል፡፡