ብሔራዊ ፈተናን ለጓደኛው ሲፈተን የተገኘው የዩኒቨርስቲ ተማሪ በእስራት ተቀጣ

73
አርባምንጭ ግንቦት 24/2010 በጨንቻ መሰናዶና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የአስረኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና ለጓደኛው ሲፈተን የተገኘው የዩኒቨርስቲ ተማሪ በአንድ ዓመት ጽኑ እስራት እንዲቀጣ መወሰኑን የጨንቻ ወረዳ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አስታወቀ። የፍርድ ቤቱ ፕሪዚዳንት አቶ ወንድወሰን አሰፋው ለኢዜአ እንደገለጹት አርባምንጭ ዩኒቨርስቲ የሶስተኛ ዓመት የስቪል ምህንድስና ተማሪው ላይ ቅጣቱ የተላለፈው ለጓደኛው ሲፈተን እጅ ከፍንጅ በመያዙ ነው፡፡ ተማሪው ወደ መፈተኛ ክፍል የገባው  ሐሰተኛ የመፈተኛ መታወቂያ በማዘጋጀት መሆኑንና ድርጊቱን  መፈጸሙን በሰጠው ቃል ማመኑን አመልክተዋል፡፡ ግለሰቡ የተያዘው የሂሳብ ፈተና ላይ መሆኑንና ቀደም ብሎ የተሰጡ ፈተናዎችንም  ጓደኛውን ወክሎ መስራቱን እንዳመነም የፍርድ ቤቱ ፕረዚዳንት አስታውቀዋል። ጉዳዩን ሲያጣራ የቆየው የወረዳው ፍርድ ቤት ዛሬ ከሰዓት በኋላ በዋለው ችሎት በተማሪው ላይ የቅጣት ውሳኔውን አሳልፏል፡፡ የራሱን ፈተና አሳልፎ በመስጠት የተጠረጠረው የትምህርት ቤቱ ተማሪ ለጊዜው አምልጦ በመሰወሩ ፖልስ ተከታትሎ ለህግ እንዲያቀርብ ፍርድ ቤቱ ትእዛዝ መስጠቱን አቶ ወንድወሰን አመልክተዋል፡፡ ግለሰቡ በጓደኛው ሰም የሰራቸው የፈተና ውጤቶችም እንዲሰረዙ ፍርድ ቤቱ ወስኗል። የጋሞ ጎፋ ዞን የብሔራዊ ፈተናዎች ኮማንድ ፖስት ሰብሳቢ  አቶ ማሔ ቦዳ ውሳኔውን በተመለከተ በሰጡት አስተያየት "ውሳኔው አስተማሪ ነው" ብሏል። የተሰወረውን ተማሪ ለህግ ለማቅረብ በሚደርገው ጥረት ኮማንድ ፖስቱ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ ገልጸዋል። ለጓደኛው ሲፈተን የተገኘው  አርባምንጭ ዩኒቨርስቲ የሶስተኛ ዓመት የስቪል ምህንድስና ተማሪው የተያዘው ትናንት እንደሆነ  ቀደም ብሎ ተገልጿል፡፡ በጋሞ ጎፋ ዞን በ86 ጣቢያዎች ሲሰጥ የቆየው የአስረኛ  ክፍል ብሔራዊ ፈተና በስኬት መጠናቀቁም ተመልክቷል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም