ህገወጥ የሰዎች ዝውውርን ለመቀነስ በጥናት የተለዩ ግኝቶች እንዲሰራባቸው ምሁራን ጠቆሙ

219

ጉባ መጋቢት 22/2011 አምራቹን ትውልድ የሚያሳጣና የሀገር ገጽታን የሚያበላሽ ህገወጥ የሰዎች ዝውውርን ለመቀነስ  በጥናትና ምርምር የተለዩ ግኝቶች እንዲሰራባቸው ምሁራን ጠቆሙ፡፡

የመዳ ወላቡ ዩኒቨርሲቲ  በህገወጥ የሰዎች ዝውውር ዙሪያ  ያዘጋጀው ሀገር አቀፍ የምርምር ጉባኤ ተካሄዷል፡፡

በዚህ ወቅት የጉባኤው ተሳታፊ ምሁራን እንደገለጹት ህገወጥ የሰዎች ዝውውር አምራቹን ኃይል ከማሳጣት ባሻገርየሀገር ገፅታንም የሚያበላሽ በመሆኑ መንስኤውን በጥናትና ምርምር የተለዩ ግኝቶች አሉ፡፡ ፡

በመዳ ወላቡ ዩኒቨርሲቲ የምጣኔ ሀብት  ትምህርት ክፍል መምህር አቶ መስፍን አብረሃም ባሌ ውስጥ የተለያዩ ወረዳዎች በወጣቶች ላይ በሚስተወለው ህገወጥ የሰዎች ዝውውር መንስኤና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ ጥናት ማድረጋቸውን አስታውቀዋል፡፡

በጥናት ግኝታቸው መሰረት ወጣቶቹ በህገወጥ መልኩ የሚሰደዱት በአብዛኛው  የተሻለ ኑሮ ፍለጋ  አስበው እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

አቶ መስፍን ወጣቶቹ ህገወጥ መንገድን ተመራጭ የሚያደርጉት በህጋዊ መልኩ የሚደረጉ የውጭ ጉዞ ላይ በቂ ግንዛቤ ስለሌላቸውና የደላሎች ተፅእኖም ከፍተኛ እንደሆነ  በጥናታቸው ለይተዋል፡፡

መንግስትና ጉዳዩ የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት የጥናት ውጤቱ የሚያሳየውን ግኝት መሰረት በማድረግ በህገወጥ የሰዎች ዝውውር አስከፊነት ላይ ተከታታይነት ያለው የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና መስጠት አለበት፡፡

"በተጓዳኝም በህጋዊ መልኩ ስለሚካሄደው የውጭ  ጉዞ ላይ በቂ ግንዛቤ በመፍጠር ችግሩን ለመቀነስ በትኩረት ሊሰራ ይገባል" ብሏል፡፡

ከወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ በዘርፉ ላይ ጥናት ያቀረቡት ዶክተር አለማየሁ አዱኛ በበኩላቸው ህገ ወጥ ስደት በርካታ ገፊና ሳቢ ምክንያቶች እንዳሉት ተናግረዋል፡፡

የኅብረተሰቡ የአመለካከትና አስተሳብ ችግሮች፣ ድህነት፣ የደላሎች ማታለያ፣ የአቻ ለአቻና የቤተሰብ ግፊትና  የፖለቲካ አለመረጋጋት  በጥናታቸው ያመላከቷቸው ናቸው፡፡

በዚህም ህገወጥ ስደትን ለመከላከል በወጣቶች የስራ እድል ፈጠራና  የደላሎች ተጽዕኖን ለመግታት የሚደረገውን ጥረት ማጠናከርና ከስደት የሚመለሱትን በፍላጎታቸው መሰረት እንዲቋቋሙ የማድረግ ተግባራት በተቀናጀ መልኩ መሰረት እንደሚጠይቅ አስረድተዋል፡፡

የመንግሥት አካላት ወጣቶች ህገወጥ ስደትን የመጀመሪያ አማራጭ እንዲያደርጉ የሚያታልሉ ደላሎችና ተባባሪዎቻቸው ላይ የሚወስደውን ህጋዊ እርምጃ መጠናከር እንዳለበት ያመለከቱት ደግሞ ከአምቦ ዩኒቨርሲቲ ጥናታቸውን ያቀረቡት መምህር በቀለ አለማየሁ ናቸው፡፡

ከዚህም  ጎን ለጎን በህጋዊ አሰራር ላይ የሚታዩ የቢሮክራሲ ውጣ ውረድና ብልሹ አሰራሮች   መፈተሽ እንደሚገባም ጠቁመዋል፡፡

የመዳ ወላቡ ዩኒቨርሲቲ የምርምር፣ ማህበረሰብ አገልግሎትና የቴክኖሎጂ ሽግግር ምክትል ፕሬዝዳንት ዶክተር ስሜነህ ቤሴ ህገወጥ የሰዎች ዝውውርና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ በባሌ ዞን የተለያዩ ወረዳዎች   ጥናት ሲያካሄድ መቆየታቸውን  አስታውሷል፡፡

ዩኒቨርሲቲው በዘርፉ ላይ ያደረገው  የጥናት ግኝቶችን መሰረት በማድረግ  የኢንተርፕሪነርሺፕ ማዕከል አቋቁመዋል፡፡

በማዕከሉ አማካኝነት በዘርፉ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመፍታት ከ2ሺህ ለሚበልጡ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች በስራ ፈጠራ እሳቤና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ በተግባር የተደገፈ ስልጠና መስጠቱን ጠቅሰዋል፡፡

ባለፉት ዓመታት በተለያዩ የትኩረት መስኮች ላይ ያተኮሩ ከ300 የሚበልጡ ችግር ፈቺ ምርምሮችና ማህበረሰብ አገልግሎት ፕሮጀክቶችን ዩኒቨርስቲው ማካሄዱንም  ዶክተር ስሜነህ አመልክተዋል፡፡

ከሀገሪቱ የተለያዩ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የተጋበዙ ተመራማሪዎች  የተሳተፉበትና ለሁለት ቀናት በተዘጋጀው  የምርምር ጉባኤው  18  ጥናታዊ ጽሁፎች ቀርበው  ውይይት ተደርጎባቸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም