የደህንነት ተቋማትን ከፖለቲካ ወገንተኝነት ለማፅዳት የተሰራው ስራ ውጤታማ ነበር

63

አዲስ አበባ መጋቢት 21/2011 ባለፈው አንድ ዓመት የደህንነት ተቋማትን ከፖለቲካ ወገንተኝነት ለማፅዳትና የተልእኮ መደራረብን ለማስቀረት የተሰራው ስራ ውጤታማ እንደነበር ተገለጸ።

የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ከመጋቢት 2010 ዓም እስከ አሁን የተገኙ ሁለንተናዊ ለውጦች ላይ ያተኮረ ውይይት ዛሬ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ አዳራሽ አካሂዷል።

በውይይቱ ወቅት የጠቅላይ ሚኒስትሩ የደህንነት ተቋማት አማካሪ አቶ ተስፋሁን ጎበዛይ ''የደህንነት ዘርፍ ሪፎርም'' በሚል ባቀረቡት ጽሁፍ ባለፈው አንድ ዓመት የአገር ደህንነት ማስጠበቂያ ተቋማት የግለሰቦች ጥቅም ማስፈጸሚያ እንዳይሆኑ የሚያስችል ስራ ተሰርቷል።

ተቋማቱን ከፖለቲካ ወገንተኝነት የማጽዳት፣ የአደረጃጀትና የተልዕኮ ማሻሻያ ማድረግ፣ ተቋማቱ በተናጥልና ሚስጥራዊ በሆነ መንገድ የሚያከናውኑትን ተግባር በጋራና በተቀናጀ መልክ እንዲፈጽሙ የማድረግ ስራ ተሰርቷል። 

እነዚህንና መሰል ችግሮችን ለመፍታት አመራሮች በጋራ እየተገናኙ እንዲሰሩና በለውጡ ዘመናዊና ብቁ የመከላከያ ሰራዊት የመገንባት ተግባር እንዲያከናወን ተደርጓል።

በተለይ የመከላከያ ሰራዊት በህዝቡ ዘንድ የነበረውን አሉታዊ አመለካካት ለመለወጥና የህዝቡ መሆኑን በተግባር ለማሳየት ተችሏል።

በተጨማሪም ለውጡ በሁሉም የደህንነት ተቋማት የአመራሩ ቁርጠኝነት ሰፊ እንደነበረ ገልጸዋል።

''የለውጡ ድሎችና የትኩረት መስክ'' በሚል ጽሁፍ ያቀረቡት በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት በሚኒስትር ዴኤታ ማዕረግ የወቅታዊ ጉዳዮች ዳይሬክተር አቶ ፍስሃ ይታገሱ እንዳሉት በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ታፍኖ የነበረውን የህዝብ ድምጽ ለመመለስ በርካታ ተግባራት ተከናውነዋል።

የፖለቲካ ምህዳሩ እንዲሰፋ፣ የታጠቁ ኃይሎች ወደ ሰላማዊ ትግል የሚገቡበትና የሚዲያ ነጻነት እንዲረጋገጥ የተከናወኑ ተግባራት ውጤታማ እንደነበሩ ተናግረዋል።

ከ10 በላይ የታጠቁ ሃይሎች ወደ አገር ውስጥ እንደገቡ፣ 45 ሺህ እስረኞች የምህረት አዋጅ ተጠቃሚ እንደሆኑ፣ ከ100 ሺህ በላይ እስረኞች  እንዲፈቱና ከ260 በላይ ሚዲያዎች፣ ጦማሪያንና ድረ-ገጾች ነጻ እንዲሆኑ ተደርጓል።

ምክትል ጠቅላይ አቃቢ ህግ ዶክተር ጌዲዮን ጢሞቲዮስ ''የፍትህና የሕግ ስርዓት ማሻሻያ ምልከታ'' በሚል ባቀረቡት ጽሁፍ ባለፉት አንድ ዓመት ዴሞክራሲ እንዲተገበርና የህግ የበላይነት እንዲከበር የሚያስችሉ ተግባራት ተከናውነዋል።

በለውጡም ሰብዓዊ መብት ጥሰት ይፈጽሙ የነበሩ ተጠያቂ የሚሆኑበት አሰራር መዘርጋት፣ በርካታ የህግ ማሻሻያ ስራዎች መስራት፣  በሽብርተኝነት የተፈረጁ ሰዎች ወደ አገር ውስጥ እንዲገቡና በርካታ እስረኞች እንዲፈቱ ተደርጓል።

እነዚህ የተጀመሩ ለውጦች እንዳይቀለበሱና ውጤታማነታቸው እንዲቀጥል ሁሉም የበኩሉን መወጣት እንዳለበት ጽሁፉ አቅራቢዎቹ ተናግረዋል።

በመድረኩ የተፎካካሪ ፓርቲ አመራሮችና ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች የተወጣጡ ግለሰቦች ተሳታፊዎች የነበሩ ሲሆን፤ ለውይይት መነሻ የሚሆኑ ጽሁፎችም ከተለያዩ ተቋማት በተወከሉ የመንግስት አመራሮች ቀርቧል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም