ኢትዮጵያ የተጎዳ ኢኮኖሚዋን ለማሻሻል አዳዲስ ወዳጆች ማፍራት ያስቻለ ዲፕሎማሲ ተግብራለች

117

አዲስ አበባ መጋቢት 21/2011 ኢትዮጵያ በከፍተኛ የብድር ጫናና የመንግስት ወጪ የተጎዳ ኢኮኖሚዋን ለማሻሻል የቀድሞዎችን ሳታስከፋ አዳዲስ ወዳጆችን ማፍራት ያስቻለዲፕሎማሲ መተግበሯ ተገለጸ።

የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ያዘጋጀውና ከመጋቢት 2010 ዓም እስከ አሁን የተመዘገቡ ሁለንተናዊ ለውጦች ላይ ያተኮረ ውይይት ዛሬ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ አዳራሽ ተካሄዷል።

በመድረኩ የተፎካካሪ ፓርቲ አመራሮችና ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች የተወጣጡ ግለሰቦች የተሳተፉ ሲሆን ፤ ለውይይት መነሻ የሚሆኑ ጽሁፎችም ከተለያዩ ተቋማት በተወከሉ የመንግስት አመራሮች ቀርበዋል።

በኢትዮጵያ የውጭ ፖሊሲ ጥናት ተቋም ምክትል ዳይሬክተር የሆኑት አቶ ሃሌሉያ ሉሌ ባለፈው አንድ ዓመት የሃብት ምንጮችን ያበራከተ፤ የነበሩ ወዳጆች ሳይከፉ አዳዲስ ወዳጆችን ማፍራት ያስቻለ የዲፕሎማሲ ስራ መከናወኑን በዚህ ወቅት ተናግረዋል።

ዓመቱ ኢትዮጵያ በውጭ አገራት ዘንድ ያላትን ገጽታ በእጅጉ ያሻሻለ ተግባር የተከናወነበት እንደነበርም አክለዋል።

መንግስት በአገር ውስጥ ይዞት የመጣውን የእርቅ፣ መግባባትና አንድነት ትርክት ወደ ውጭ ይዞ መውጣቱ ደግሞ ለዲፕሎማሲው ስኬት ዋነኛ  ምክንያት መሆኑን ነው ያብራሩት።

የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ጉዞን በተመለከተ ገለጻ ያደረጉት የጠቅላይ ሚኒስትሩ ከፍተኛ የኢኮኖሚ ፖሊሲ አማካሪ አቶ ማሞ እስመለዓለም-ምህረት አዲሱ አስተዳደር የተረከበው ኢኮኖሚ በከፍተኛ አረንቋ የተተበተበ እንደነበር ያወሳሉ።

ከግዙፍ ፕሮጀክቶች ግንባታ ጋር በተያያዘ አገሪቱ ከፍተኛ ወለድ የሚከፈልበት ብድር ሰለባ እንደሆነች ገልጸው ፤ የብድር ጫናው ከኢትዮጵያ ጥቅል አገራዊ ምርት የ54 በመቶ ድርሻ አለው ብለዋል።

ይህም በአገሪቱ ከተመዘገበው የኢኮኖሚ እድገት ውስጥ የመንግስት ኢንቨስትመንት ከፍተኛውን ድርሻ እንዲይዝ አድርጎታል ነው ያሉት።

እንዲህ ባለው አዘቅት ውስጥ በየዓመቱ ሁለት ሚሊዮን ስራ ፈላጊዎች ኢኮኖሚውን እንደሚቀላቀሉም አውስተዋል።

ባለፈው አንድ ዓመት የማክሮ ኢኮኖሚ መዛባቱን ለማስተካካል የተለያዩ ተግባራት እንደተከናወኑ የገለጹት አቶ ማሞ ፤ አዳዲስ ፕሮጀክቶችን ከማስጀመር ይልቅ የተጀመሩትን ማጠናቀቅ በሚል መርህ የመንግስትን የበጀት ጉድለት ከሶስት በመቶ በታች ማድረስ መቻሉን ተናግረዋል።

በተጠቀሰው ጊዜ ከተለያዩ ለጋሽ አገሮችና ተቋማት ከ3 ነጥብ 2 ቢሊዮን ዶላር በላይ ሃብት ማሰባሰብ መቻሉን በመጠቆም።

ስራን በቀላሉ መጀመር የሚያስችሉ አሰራሮችን በመተግበር በርካታ ዜጎችን ወደ ስራ ለማስገባት እየተሰራ መሆኑንም አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም