ህንድ በአፍሪካ የምታደርገው ተሳትፎ እያደገ መጥቷል

57

አዲስ አበባ መጋቢት 21/2011 ህንድ ከአፍሪካ ጋር ያላት ወዳጅነትና ሁለንተናዊ ግንኙነት እየተሻሻለ መምጣቱን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ማርቆስ ተክሌ ተናገሩ።

የህንድ ዓለም አቀፍ ጉዳዮች ካውንስል ያዘጋጀው የህንድ አፍሪካ ጉባኤ ላይ ሚኒስትር ዴኤታው እንደተናገሩት ህንድ ከአፍሪካ ጋር ያላት መዋቅራዊ ተሳትፎ እያደገ መጥቷል።

በኢትዮጵያና ህንድ መካከል ያለው ሁለንተናዊ የልማት ትብብር በንግድ፣ ኢንቨስትመንት፣ ቀላል ብድርና የቴክኒክ ድጋፍ ላይ ያተኮረ ነው።

እንደ አውሮጳውያን አቆጣጠር በ2017 በሁለቱ አገሮች መካከል የነበረው የንግድ ልውውጥ 1 ነጥብ 37 ቢሊዮን ዶላር እንደነበርና ህንድ ለኢትዮጵያ የስኳር ፕሮጀክቶችና የገጠር ኤሌክትሪክ ማስፋፋፊያ 1 ነጥብ 1 ቢሊዮን ዶላር የብድር ድጋፍ ማድረጓን ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ የህንድ አምባሳደር አኑራግ ስሪቫስታቫ እንደተናገሩት አገራቸው በተለይም በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት ከአፍሪካ አጋሮቿ ጋር ተባብራ ለመስራት ቁርጠኛ ነች።

በቀጣይም ህንድ በረጅም ጊዜ የሚመለስ የ10 ቢሊዮን ዶላር ብድር፣ ለተለያዩ ፕሮጀክቶች የሚውል 600 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ እና 50 ሺህ የትምህርት እድልና ስልጠና እንደምትሰጥም ተናግረዋል።

አምባሳደሩ እንደተናገሩት ህንድ እስከ አሁን ለተለያዩ ፕሮጀክቶች የሚያግዝ ዘጠኝ ቢሊዮን ዶላር የረጅም ጊዜ ብድር ሰጥታለች።

በህንድና አፍሪካ መካከል ያለው የንግድ ልውውጥ 63 ቢሊዮን ዶላር የደረሰ ሲሆን ባለፈው ዓመት ብቻ የ22 በመቶ ዕድገት አሳይቷል። 

በአፍሪካ 54 ቢሊዮን ዶላር መዋዕለ-ነዋይ በማፍሰስ አምስተኛ ደረጃ ላይ እንደምትገኝም አምባሳደሩ ጠቅሰዋል።

ህንድ ከአፍሪካ ጋር ያላትን ፖለቲካዊ፣ ምጣኔ ሀብታዊ፣ ስትራቴጂካዊ፣ ባህላዊና ሌሎች ተሳትፎዎቿን ለማጠናከር ባዘጋችው ጉባኤ ላይ ከ10 የሰሜን አፍሪካና የአፍሪካ ቀንድ አገራት የተውጣጡ ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።

ጉባዔው የአፍሪካ ጉዳዮችን በተመለከተ ተመራማሪዎች፣ ፖሊሲ አውጪዎችና ምሁራን ሊጠቀሙባቸው የሚችሉ ግብዓቶችን ለማግኘት እንደሚረዳ ተመልክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም