በክልሉ በማዕድን ልማት የተሰማሩ ባለሃብቶች በዘርፉ የሚታዩ ማነቆዎች እንዲፈቱላቸው ጠየቁ

136

አሶሳ  መጋቢት 21/2011 በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የሚገኘውን የማዕድን ሃብት በሚገባ አልምቶ ለሀገር ጥቅም ለማዋል በዘርፉ የሚታዩ ማነቆዎች ሊፈቱ ይገባል ሲሉ ባለሃብቶች ጠየቁ፡፡

በዘርፉ የተሰማሩ ባለሀብቶችና መንግስታዊ አካላት ተቀራርበው መስራት በሚችሉበት ሁኔታ ላይ ያተኮረ ውይይት በአሶሳ ከተማ ተካሂዷል፡፡

በውይይቱ ከተሳተፉት ባለሃብቶች መካከል የፋየርዶውስ እምነበረድ ማምረቻ ድርጅት ኃላፊ አቶ አወል አሊ ድርጅታቸው በክልሉ በአምስት ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር የእምነበረድ ልማት ሥራ ውስጥ መግባቱን ገልጸዋል፡፡

የድርጅቱ የሥራ እንቅስቃሴና ምርታማነት እያደገ መምጣቱን ጠቁመው በቅርቡ የክልሉ መንግስት በትላልቅ ኢንቨስትመንቶች የተያዙ መሬቶች ወደ 20 ሄክታር ዝቅ እንዲል ማድረጉ የድርጅቱን ሥራ ስለሚጎዳ ዳግም እንዲታይ ጠይቀዋል።

የኑቢያ ወርቅ አምራች ድርጅት ሥራ አስኪያጅ አቶ ወንድሙ ዮሐንስ በበኩላቸው ድርጅታቸው በ30 ሚሊዮን ብር ካፒታል በመተከል ዞን የወርቅ ፍለጋ እያካሄደ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

" ከፈቃድ አሰጣጥ ጀምሮ ተያያዥ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ከፌደራል እስከ ወረዳ ያለው የተጓተተ አሰራር ድርጅቱንና ሠራተኞችን ያለሥራ እንዲቀመጡ በማድረግ ለኪሳራ ዳርጓል" ብለዋል፡፡

በክልሉ የሚገኘውን የማዕድን ሃብት በሚገባ አልምቶ ለሀገር ጥቅም ለማዋል በዘርፉ የሚስተዋሉ ችግሮችን በመፍታት ምቹ ሁኔታ እንዲፈጠር ጠይቀዋል።

በአሥር ሚሊዮን ዶላር እምነበረድ የሚያመርተውና የሚያቀነባብረው የሻንዶንግ ሚሊዮን ስቶንስ ዋና ሥራ አስኪያጅ ሊን ጂን በበኩላቸው ለኢንቨስትመንት ስራው ከ338 ሄክታር በላይ መሬት ከክልሉ መረከባቸውን ተናግረዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት ምርት ለመጀመር የውሃ ጉድጓድ፣ የመንገድና የማምረቻ ቦታ ግንባታ ሥራዎች መጠናቀቃቸውን ጠቅሰው ወደልማቱ ለመግባት መንግስት የኤሌክትሪክ ኃይል፣ የመገናኛና ሌሎች መሠረት ልማቶችን እንዲያሟላ ጠይቀዋል፡፡

በክልሉ በ1 ነጥብ  5 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር የእምነበረድ ማቀነባሪያ ለመትከል ለስድስት ወራት የቦታ ጥያቄ ቢያቀርቡም ሰሚ ማጣቸውን የተናገሩት ሌላው ባለሃብት ደግሞ የስሪ ኤም ማርብልና ቴራዞ ማምረቻ ዋናሥራ አስኪያጅ አቶ መስፍን ሙሉጌታ ናቸው፡፡

"የክልሉን ማዕድን ሃብት በሚገባ በማልማት ለሃገር ኢኮኖሚ ዕድገት እንዲውል መንግስት በዘርፉ የሚስተዋሉ ችግሮችን ሊፈታ ይገባል" ብለዋል፡፡

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሃሰን በበኩላቸው "በክልሉ መሠረተ ልማት ቢስፋፋም ማዕድን አምራች ባለሃብቶች ጥሬ ምርት ወደማዕከል ከመላክ ውጪ እሴት ጨምረው ለገበያ ማቅረብ አልጀመሩም" ብለዋል፡፡

ይህም የአካባቢው ህዝብ ከሃብቱ ተጠቃሚ እንዳላደረገው ገለጸው፣ ባለሃብቶች የምርት ማቀነባበሪያ በአካባቢው በመትከል የሥራ ዕድል ሊፈጥሩ እንደሚገባ አስገንዝዋል፡፡

በክልሉ ለማዕድን ማምረት ስራ እስከ 1 ሺህ ሄክታር ቦታ በኢንቨስትመንት ስም ወስደው ለዓመታት ሳያለሙ የቆዩ ባለሀብቶች መኖራቸውን የገለጹት አቶ አሻድሊ በዚህ ምክንያት ለኢንቨስትመንት የሚሰጥ መሬት ከ20 ሄክታር እንዳይበልጥ መወሰኑን አስረድተዋል፡፡

ለማዕድን ኢንቨስትመንት የመሬት ስፋት ሳይሆን ሃብቱን በጥናት መለየት አስፈላጊ መሆኑን አመልክተው "ባለሃብቶች በያዙት 20 ሄክታር መሬት ችግሮች ካጋጠሟቸው ምትክ መሬት ሊያኙ ይችላሉ ብለዋል"፡፡

ከአገልግሎት አሰጣጥ ጋር በተያያዘ የሚስተዋሉ ችግሮች መኖራቸውን ያመኑት ርዕሰ መስተዳድሩ የጸጥታ ችግሮችን ጨምሮ ሌሎችንም ማነቆዎች ለመፍታት የተዘጋጀ የህዝብ ንቅናቄ መድረክ በቅርቡ እንደሚካሄድ አመልክተዋል፡፡

የማዕድንና ነዳጅ ሚኒስትሩ ዶክተር ሳሙኤል ኦርቃቶ በበኩላቸው የፌደራል መንግስት ለማዕድን ልማት ትኩረት መስጠቱን ገልጸዋል፡፡

ዘርፉ የሃገሪቱን ኢኮኖሚ 30 በመቶ እንዲሸፍን ለማድረግ በተለይ በወርቅ ምርት ችግሮችና መልካም አጋጣሚዎች ላይ ዝርዝር ጥናት እየተካሄደና በቅርቡ እንደሚጠናቀቅም ጠቅሰዋል፡፡

"በተጨማሪም መሠረተ ልማትን ጨምሮ ለማዕድን ልማት እንቅፋት የሆኑ ችግሮችን ለመፍታት ከሚመለከታቸው የፌደራልና የክልል ተቋማት ጋር በትኩረት እየሠራን ነው" ብለዋል፡፡

"አሁን በማዕድን ልማት ዘርፍ የሚታዩ ችግሮች ጊዜያዊና በቅርቡ የሚፈቱ ናቸው" ያሉት ዶክተር ሳሙኤል፣ ባለሃብቱ የማዕድን ሀብቱን እሴት ጨምሮ ለገበያ በማቅረብ ሃብቱ በዘላቂነት ጥቅም ላይ ለማዋል እንደሰራ አሳስበዋል፡፡

ለግማሽ ቀን በተካሄደ የውይይት መድረክ ላይ ከ50 የሚበልጡ ማዕድን አምራች ባለሃብቶች፣ ማህበራትና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተሳተፈዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም