ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ እያስተላለፉት ያለው መልእክት አገራዊ አንድነትን የሚያበስር ነው- ቅዱስ ሲኖዶስ

99
አዲስ አበባ ሚያዝያ 29/2010 ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አሕመድ የሚያስተላልፉት መልዕክት አገራዊ አንድነትን የሚያበስር በመሆኑ ቤተ ክርስቲያኗ በአክብሮት እንደምትቀበለው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ አስታወቀ። ለተጀመረው ጥረት አካል በመሆንም የበኩሏን ድርሻ እንደምታበረክት ተገልጿል። ቅዱስ ሲኖደሱ ከሚያዝያ 23 ቀን 2010 ዓ ም ጀምሮ ሲያካሂድ የነበረውን የሰባት ቀናት ርክበ ካህናት ጉባኤ አጠናቆ ዛሬ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል። ጋዜጣዊ መግለጫውን የሰጡት ብጹዕ ወቅዱስ አባ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ዘኢትዮጵያ "ቅዱስ ሲኖደሱ ሲያካሂድ በነበረው ጉባኤ ለአገሪቷና ለቤተ ክርስቲያኗ የሚበጁ ውሳኔዎችን አሳልፏል" ብለዋል። ምልዓተ ጉባኤው ከግንቦት 2009 ዓ.ም እስከ ግንቦት 2010 ዓ.ም በቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤና በቋሚ ሲኖዶስ በተላለፉ ውሳኔዎች አፈጻጽም ላይ ተወያይቶ አስፈላጊውን መመሪያ በመስጠት ማጽደቁን ተናግረዋል። ምልዕተ ጉባኤው "ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ከበዓለ ሲመታቸው ጀምሮ የሚያስተላልፉት መልዕክት አገራዊ አንድነትን፣ ሰላምና መረጋጋትን የሚያበስር በመሆኑ ቤተ ክርስቲያኗ እንደምትደግፈው" ገልጸዋል። የጠቅላይ ሚኒስትሩ ንግግር "አገራዊ አንድነትን፣ ፍቅርና ትህትናን የሚያስተምር፣ ሰላምና መረጋጋትን የሚያበስር፣ የሩቅና ቅርቡን የሚያስተባብር መንግስታዊ ኃላፊነት የተሞላበት መልእክት በመሆኑ የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ በአክብሮት ተቀብሎታል" ነው ያሉት። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በክልሎች እየተዘዋወሩ በወንድማማች ሕዝቦች መካከል የተፈጠረ መቃቃር ተወግዶ ሰላምና መረጋጋት እንዲሰፍን መመሪያ በመስጠት እያደረጉት ያለውን ጥረት ቅዱስ ሲኖዶሱ በሙሉ ልብ እንደደገፈው ገልጸዋል። የጥረቱ አካል በመሆንም የበኩሉን ድርሻ ለማበርከት ምልዓተ ጉባኤው መስማማቱን አረጋግጠዋል። የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ ቤተ ክርስቲያኗ በገንዘብም ሆነ ሕዝቡን በማስተባበር ድጋፍ ስታደርግ የቆየች መሆኗን የገለጹት ፓትርያርኩ ፤ በቀጣይም የማስተባበርና የእርዳታ ገንዘብ የማሰባሰብ አገራዊ ግዴታዋን እንደምትወጣ አረጋግጠዋል። ወጣቱ አገሩን፣ ሀይማኖቱን፣ ባህሉን፣ ቋንቋውን፣ ስርዓትና ትውፊቱን በመጠበቅና ስራ የመፍጠር ባህሉን በማጎልበት አገሩን እንዲያለማ ቅዱስ ሲኖዶሱ በመግለጫው 'አደራ' ብሏል። ይህ በእንዲህ እንዳለ ቅዱስ ሲኖዶሱ በተለያዩ ምክንያቶች ለስራ ዝውውር እንዲደረግላቸው ጥያቄ ያቀረቡ ሊቃነ ጳጳሳትን ጉዳይ በማጥናት ዝውውሩ እንዲፈጸም መወሰኑን ተናግረዋል። ወላጆቻቸውን በሞት አጥተው ሰብሳቢ ያሌላቸው ህጻናትን በማሳደግና በማስተማር ላይ የሚገኘው የቤተ ክርስቲያኗ የህጻናትና ቤተሰብ ጉዳይ ድርጅት ስራውን አጠናክሮ እንዲቀጥል መመሪያ መስጠቱንም ገልጸዋል። በሌላ በኩል በቅርቡ ኢትዮጵያን የጎበኙት የእስራኤሉ ፕሬዚዳንት ሬዩቭን ሪቭሊን ቅዱስ ሲኖዱሱ ጉባኤውን በጀመረበት ዕለት ቤተ ክርስቲያኗን መጎብኘታቸውንና የጋራ ውይይት ማድረጋቸውን አስታውሰዋል። የዴር ሱልጣን ገዳም በተመለከተ ለግማሽ ሰዓት ያህል ውይይት ማድረጋቸውን ገልጸው፤ በኢየሩሳሌም የሚገኙ የኢትዮጵያ ገዳማት በሙሉ እንደሚታደሱ ፕሬዚዳንቱ መናገራቸውን ገልጸዋል። በተለይም በቅርቡ የመፍረስ አደጋ የደረሰበት የቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን ቅድሚያ ተሰጥቶት እንደሚታደስ የቃል ተስፋ መስጠታቸውን ነው ያብራሩት።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም