የቀድሞ የሶማሌ ክልል ፕሬዚዳንት የቀረበባቸው ክስ መሰረታዊ የክስ አቀራረብ ስርአትን የጣሰ እንደሆነ ገለጹ

85

አዲስ አበባ መጋቢት 21/2011 የቀድሞ የሶማሌ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ አብዲ ዑመር ሙሐመድ የቀረበባቸው ክስ መሰረታዊ የክስ አቀራረብ ስርአትን የጣሰ መሆኑን አስታወቁ።

በአቶ አብዲ የክስ መዝገብ ውስጥ ከተካተቱት ስድስት ሰዎች መካከል ሶስቱ ትናንት ለፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት የክስ መቃወሚያቸውን አቅርበዋል።

በዚህ መሰረት አቶ አብዲ ''የቀረበብኝ ክስ መሰረታዊ የክስ አቀራረብ ስርዓትን የጣሰ ነው፣ ክሱ የወንጀል ተሳትፎዬን አያሳይም፣ የሄጎ ቡድን አባላት ተብለው በዐቃቤ ሕግ ክስ የቀረበው የትኛውን ህዝብ፣ ወታደርና ሽፍታ እንደሚወክሉ አያሳይም'' በማለት መቃወሚያቸውን አቅርበዋል።

''በተጨማሪም የትጥቅ አመፅ በህገ- መንግስቱ በተወከሉ ባለስልጣናት ላይ ተነስቷል እንዲሁም ሽፍቶችን፣ ወታደሮችን ወይም ህዝቡን አደራጅቶ መርቷል'' የሚል ሀሳብ በክሱ አልተገለፀም በማለት በጽሑፍ ባቀረቡት መቃወሚያ አስረድተዋል።

''መሳሪያ ያስታጠኩና ያነሳሳሁ ስለመሆኑ ክሱ አያመላክትም፣ የእርስ በርስ ጦርነት አስነስቷል የሚለው ማን ከማ ጋር ባደረገው ጦርነት እንዳስነሳሁም አልተገለፀም'' ብለዋል።

''በወቅቱ በተለያዩ ክልሎች ግጭት፣ ሞትና የንብረት ውድመት ደርሷል'' በማለት የሌሎች ክልሎች አመራሮች ሳይጠየቁ እሳቸው ክልሉን በተረጋጋ ሁኔታ ይመሩ እንደነበር ገልጸዋል።

''እኔን ብቻ ተጠያቂ ማድረግ በህገ - መንግስቱ አንቀፅ 25 የተቀመጠውን የእኩልነት መብት መጋፋት ነው፣ የቀረበው ክስ የተሟላ አይደለም በመሆኑ ክሱ ውድቅ እንዲደረግ ካልሆነም ተሻሽሎ እንዲቀርብ'' በማለት ፍርድ ቤቱን ጠይቀዋል።

2ኛ ተከሳሽ ራህማ መሐመድ በበኩላቸው ''የዐቃቤ ህግ የክስ ዝርዝር ከህጉ ጋር አይጣጣምም፣ ፍርድ ቤቱ ጉዳዩን የማየት ስልጣን የለውም፣ ከሌሎች ተከሳሾች ጋር በአንድነት መከሰሴ አግባበብነት የለውም'' በማለት መቃወሚያቸውን አቅርበዋል።

''ዐቃቤ ህግ ያቀረበው ክስ ወንጀሉ የተፈፀመበትን ቦታና ጊዜ በትክክል አይገልጽም'' በማለት የቀረበባቸው ክስ ውድቅ እንዲደረግ ወይም ተሻሽሎ እንዲቀርብ ጠይቀዋል።

3ኛ ተከሳሽ አብዱራዛቅ ሰሀኒ ደግሞ ''የተከሰስኩበት ጉዳይና የወንጀል ድርጊት ተለይቶ ያልቀረበና ክሱ ግልፅኝነትት የጎደለው ነው፣ የኔ ጉዳይ ከሌሎች ተከሳሾች ተነጥሎ ሊታይልኝ ይገባል'' በማለት ፍርድ ቤቱን ጠይቀዋል፡፡

በሌላ በኩል 33ኛ ተከሳሽ ጉደሌ አቦል እና 34ኛ ተከሳሽ ወርሰሜ ሸህ አብዲ ክስ እስካሁን በአስተርጓሚ እጦት ምክንያት በንባብ ያልተሰማ መሆኑ ተገልጾ በአሁኑ ወቅት ግን አስተርጓሚ የተመደበ በመሆኑ ጠበቃቸው ባሉበት እንዲነበብላቸው ጠይቀዋል፡፡

ከዚህ ቀደም የካቲት 8 ቀን 2011 ዓ.ም የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት የቀድሞ የሶማሌ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ አብዲ መሐመድ ያቀረቡትን አቤቱታ ውድቅ ማድረጉ ይታወሳል።

ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ አቶ አብዲ መሐመድን ጨምሮ በ47 የክልሉ የሥራ ኃላፊዎች ላይ ጥር 22 ቀን 2011 ዓ.ም ክስ መስርቷል። ክስ ከተመሰረተባቸው መካከል ስድስቱ በቁጥጥር ስር የዋሉ ሲሆን 41 ተከሳሾች አልተያዙም።

ተከሳሾቹ ከሐምሌ 26 እስከ 30 ቀን 2010 ዓ.ም ጅግጅጋ ከተማን ጨምሮ በክልሉ የተለያዩ ዞኖችና ወረዳዎች በፈጠሩት ግጭት 59 ሰዎች እንዲገደሉ አድርገዋል ሲል ዓቃቤ ሕግ በክስ መዝገቡ አስፍሯል።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን፣ የመንግሥት ተቋማት፣ የግለሰቦች ቤቶችና የተለያዩ የንግድ ተቋማት ተቃጥለው እንዲወድሙ በማድረግ ከ412 ሚሊዮን ብር በላይ ጉዳት በማድረስም ክስ ተመስርቶባቸዋል።

በክልሉ የሚኖሩ ሌሎች ብሔር ብሔረሰቦች ተፈናቅለው እንዲሰደዱ ማድረጋቸውም ከቀረበባቸው ክስ መካከል ተጠቃሽ ነው።

አቃቤ ሕግ በእነዚህና ሌሎች ወንጀሎች ላይ 213 ምስክሮች እንዳሉት ለፍርድ ቤቱ አሳውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም