በአገር አቀፉ የትምህርት ቤቶች ስፖርት ውድድር ትግራይ በቢስክሌትና በክብደት ማንሳት ውድድሮች አሸነፈ

62

መቀሌ መጋቢት 21/2011 በመቀሌ ከተማ  ስምንተኛ ቀኑን በያዘው ሀገር አቀፍ የትምህርት ቤቶች ስፖርታዊ ውድድር የትግራይ  ክልል በቢስክሌትና በክብደት ማንሳት አሸናፊ ሆነ።

ዛሬ በተካሄደውና የአምስት ክልሎች ተወዳዳሪዎች በተሳተፉበት 40 ኪሎ ሜትር የሸፈነ የወንዶችና ሴቶች ቢስክሌት ውድድር የትግራይ ብስክሌተኞች ከአንደኛ እስከ ስድስተኛ ደረጃን በመያዝ አጠናቀዋል።

ለውድድሩ ከተዘጋጁት ስድስት ሜዳሊያዎች አምስቱን የትግራይ ክልል ተወዳዳሪዎች ወስደዋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ተወዳዳሪዎች አንድ ሜዳሊያ በማግኘት ሁለተኛ ደረጃ ይዘዋል፡፡

በተመሳሳይ ርቀት በተካሄደ የሴቶች ቢስክሌት ውድድር የትግራይ ሴት ተወዳዳሪዎች ከአንደኛ እስከ ሶስተኛ ደረጃ በመውጣት ተሸላሚ ሆነዋል፡፡

በወንዶች 85 ኪሎ ግራምና በሴቶች 52 ኪሎ ግራም ክብደት ማንሳት ውድድር ከተዘጋጁ ስምንት ሜዳሊያዎች ስድስቱን የትግራይ ክልል በመውሰድ አንደኛና ሁለተኛ ደረጃን በመያዝ አሸናፊ ሆኗል፡፡

ድሬደዋና የአማራ ክልል ሁለቱም እኩል አንድ አንድ ሜዳሊያ በመያዝ ሶስተኛ ደረጃ ይዘው አጠናቅቀዋል፡፡

ዛሬ ስምንተኛ ቀኑን በያዘው አገር አቀፍ የትምህርት ቤቶች ውድድር እስካሁን በተካሄዱ ውድድሮች ኦሮሚያ 109 ሜዳሊያዎች በመሰብሰብ መሪነቱን እንዳስጠበቀ ነው፡፡

አማራ ክልል በ92 ሜዳሊያዎች ሁለተኛ ደረጃ ሲይዝ፣ የትግራይ ክልል በ67 ሜዳሊያዎች ሶስተኛ ደረጃን ይዞ እየተከተለ ነው፡፡

እየተካሄደ ባለው አገር አቀፍ የትምህርት ቤቶች ውድድር 3 ሺህ 500 ስፖርተኞች በ20 የስፖርት ዓይነቶች ውድድራቸውን እያካሄዱ ነው።

ውድድሩ መጋቢት 29 ቀን በደማቅ ስነ ስርዓት ይጠናቃል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም