በሚቀጥለው አመት 100 ተማሪ እንኳን ቢላክልን የምናስገባበት የለም-የጂንካ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት

79

አዲስ አበባ መጋቢት 21/2011 የመማሪያ ክፍሎች ግንባታ እስካሁን ባለመጀመሩ የጂንካ ዩኒቨርሲቲው በ2012 አዲስ ተማሪዎችን ቀድሞ የመቀበል እድሉ አናሳ እንደሆነ የዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር ገብሬ ይንቲሶ አስታወቁ።

እስካሁን ዩኒቨርሲቲው ተቀብሎ የሚያስተምራቸውን ተማሪዎች በአንድ የመማሪያ ህንጻ እያስተናገደ ሲሆን ተጨማሪ ግንባታ ማካሄድ ካልቻለ በሚቀጥለው ዓመት ተማሪዎችን ለመቀበል እንደሚቸገርም ጠቁመዋል።

ዩኒቨርሲቲው ተማሪዎችን ተቀብሎ እያስተማረ ቢሆንም ዘርፈ ብዙ ችግሮች ውስጥ እንደሚገኝ ተጠቁሟል።

የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ''ግንባታዎች የሚያከናውነው ጨረታ ወጥቶ ሳይሆን በኮንስትራክሽን በተመለከተ ሃላፊነት ያለበት የመንግስት ተቋም ቁርጥ ዋጋ አጽድቆ በመሆኑ የግንባታ መዘግየት አጋጥሞኛል'' ብሏል።

ጂንካ ዩኒቨርሲቲ በ2008 ዓ.ም ተገንብተው በ2010 ዓ.ም ወደ ስራ ከገቡ 11 አዳዲስ ዩኒቨርሲቲዎች መካከል አንዱ ነው።

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ እንደገለጹት፤ ከመማሪያ ክፍሎች ችግር በተጨማሪ የሽንት ቤት ፍሳሽ ማስወገድ፣ የላቦራቶሪ ግብዓት፣ የተማሪዎች ማደሪያ እና የመምህራን ቤት ችግር የዩኒቨርሲቲውን የመማር ማስተማር ሂደት እየፈተኑት ይገኛሉ።

የመማሪያ ክፍሎችን ለማሟላት እስካሁን የተጀመረ ግንባታ ባለመኖሩ ዩኒቨርሲቲው በ2012 ዓ.ም ተማሪዎችን ለመቀበል እንደሚቸገር ጠቁመው በቀሪው ጊዜ ግንባታ ጀምሮ ለማከናወን አዳጋች መሆኑን ገልጸዋል።

የመማሪያ ክፍል እጥረቱ ዩኒቨርሲቲው የሚከፍታቸውን 14 የትምህርት ዓይነቶች እንዳይከፍት እንቅፋት እንደሚሆንበትም ተናግረዋል።

እንደ ፕሮፌሰር ገብሬ ገለጻ፤ በዩኒቨርሲቲው የተካሄዱ ግንባታዎች የምህንድስና ክፍተት የውሃ መስመርና የኤሌክትሪክ መስመር የተገናኙበትና ውሃ የሚያንጠባጥቡ ናቸው።

ከዚህም ሌላ የሽንት ቤት መጠባበቂያ ጉድጓድ (ሴፍቲክ ታንክ) ጠባብ በመሆኑ ሽንት ቤት ቶሎ ቶሎ እየሞላ ዩኒቨርሲቲው ከባድ ችግር ውስጥ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።

ሴፕቲክ ታንኩ አነስተኛ መሆን በየቀኑ ቆሻሻው እየተመጠጠ ወደወንዝ ይገባል ይህ ደግሞ የወንዝ ውሃን ለመጠጥ የሚጠቀሙ የህብረተሰብ ክፍሎች ላይ ተጨማሪ ጉዳት ያደርሳል።

የማጣራት ስራ ይሰራል ቢባልም ይህም ምንም ያልተጀመረ እንደሆነ ተናግረዋል።

ዘንድሮው የተጀመሩ ሶስት የተማሪዎች ማደሪያ ህንጻዎች ባለመጠናቀቃቸው ለተማሪዎች ማደሪያነት የሚያገለግል ጊዜያዊ አዳራሽ ተጀምሮ ባለመጠናቀቁ ለአራት ተማሪዎች ብቻ የሚሆነውን ማደሪያ ክፍል ስድስት ተማሪዎች እንዲያስተናግድ መደረጉን ተናግረዋል።

ከግንባታ መሰረተ ልማት በተጨማሪ ዩኒቨርሲቲው የላቦራቶሪ ግብዓት አለመሟላትና የመምህራን መኖሪያ በወቅቱ ባለመሰራቱ መምህራኑ ተረጋግተው እንዳያስተምሩ ማድረጉ ተደራራቢ ችግር መሆናቸውን ገልጸዋል።

የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ችግሩን በተመለከተ ለኢዜአ በሰጠው ምላሽ ችግሩን እንደሚያውቀውና መፍትሄ ለመስጠት እየሞከረ እንደሚገኝ ገልጿል።

በሚኒስቴሩ የ11 ዩኒቨርሲቲዎች ግንባታ ፕሮጀክት ጽህፈት ቤት ዋና ስራ አስኪያጅ ዶክተር ከተማ መስቀላ እንዳሉት፤ በ2008 ዓ.ም የተጀመረው የመጀመሪያው ዙር የዩኒቨርሲቲዎቹ ግንባታ የተሳካ ቢሆንም በበጀት እጥረት የተነሳ ሁለተኛው ዙር ተጓትቷል።

ግንባታ የሚካሄደው ጨረታ ወጥቶ ሳይሆን በቁርጥ ዋጋ መሆኑን የገለጹት ዶክተር ከተማ የኮንስትራክሽን ቁጥጥር የሚያደርገው አካል ዋጋ ቆርጦ እስኪያጸድቅ ድረስ መዘግየት ማጋጠሙን ጠቁመዋል።

የጂንካ ዩኒቨርሲቲ የመማሪያ ክፍል ችግርም በ11ዱም አዳዲስ ዩኒቨርሲቲዎች ላይ ያለ ችግር እንደሆነ አንስተዋል።

ችግሩን ቶሎ ቀርፎ የዩኒቨርሲዎችን ቅበላ በተማሪዎች መግቢያ ወቅት ለማድረግም የተቋራጭ ልየታ ስራው የተጠናቀቀ ሲሆን ተመኑ ሲፀድቅ ወደ ስራ እንደሚገባ ነው የገለጹት።

ዩኒቨርሲቲዎቹ ጥቅምት ላይ መቀበል እንዲችሉ ባለው ሰባት ወራት ላይጠናቀቅ ይችላል የሚል ፍርሃት እንዳላቸው ገልጸው በተቻለ ቅልጥፍና ለመስራት ጥረት እንደሚደረግ ግን አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም