በባሌ በግብርና ኢንቨስትመንት የተሰማሩ ባለሀብቶች በቴክኖሎጂ ሽግግርና በሥራ ዕድል ፈጠራ ለውጥ አላመጡም

169

ጎባ  መጋቢት 21/2011 በባሌ ዞን በግብርና ኢንቨስትመንት የተሰማሩ ባለሀብቶች በቴክኖሎጂ ሽግግርና በሥራ ዕድል ፈጠራ መስኮች ላይ ባለመሥራታቸው ለውጥ እንዳላመጡ የጋሰራና ጊኒር ወረዳ አርሶ አደሮችና ወጣቶች ቅሬታቸውን ገለጹ።

የዞኑ ኢንቨስትመንት ጽህፈት ቤት በዞኑ በኢንቨስትመንት ዘርፍ የሚታዩ ተግዳሮቶችን ለመፍታት እየሰራሁ ነው ይላል፡፡

አርሶ አደሮቹና ወጣቶቹ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንዳስረዱት ባለሀብቶቹ በመስኮቹ የሚያደርጉት እንቅስቃሴ አካባቢውን ይለውጣል ተብሎ ቢታመንበትም የሚጠበቀውን ያህል ሆኖ አላገኙትም።

በጊኒር ወረዳ የምስራ ቀበሌ የሚኖረው ወጣት ሐሰን ከማል ከባለሀብቶቹ  ከመሬታቸው ተቀንሶ የተሰጠው የግብርና ቴክኖሎጂን ለአካባቢው አርሶ አደሮች በማስተላለፍ ተጠቃሚ ያደርጋሉ ተብሎ እንደነበር ያስታውሳል፡፡

አሁን ባለው ሁኔታ ባለሀብቶች ከአርሶ አደሩ ያነሰ ምርት መሰብሰባቸው የተባለላቸውን ያህል አለመሆናቸውን ያሳያል ብሏል፡፡

በአካባቢያቸው በግብርና ኢንቨስትመንት ስም የተወሰደ የእርሻ መሬት ያለአግባብ ታጥሮ መቀመጡን የተናገሩት ደግሞ በወረዳው የሀረዋ ቀበሌ አርሶ አደር አብዱልቃድር መሐመድ ናቸው፡፡

“አባቶቻችን አርሰውና ለእንስሳቶቻቸው ግጦሽ ሲጠቀሙበት የነበረውን የመሬት ይዞታቸውን ለልማቱ የለቀቁት ልጆቻቸው ከልማቱ ይጠቀማሉ በሚል እምነት ነው” ያለው ደግሞ የጋሰራ ወረዳ የዲንኪቲ ቀበሌ ነዋሪ ወጣት አብዱረህማን ሰዒድ ነው፡፡

ባለሀብቶቹ የራሳቸውን ጥቅምና ፍላጎት ብቻ መሠረት ያደረጉ ከመሆናቸውም በላይ፣የአካባቢውን ወጣቶች በጫኝና አውራጅ ሥራ እንኳ ተደራጅተው እንዳይሰሩ ሠራተኞች ከሌላ ቦታ አምጥተው እንደሚያሰሩ ተናግረዋል።

የዞኑ ኢንቨስትመንት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ተስፋዬ ደምሴ በበኩላቸው በዘርፉ የሚታዩ ተግዳሮቶችን ደረጃ በደረጃ ለመፍታት እየተሰራ መሆኑን ገልጸው፣በተለይም መሬት ወስደው ከልለው ባስቀመጡ ባለሀብቶች ላይ እርምጃ መወሰዱን ተናግረዋል፡፡

ጽህፈት ቤቱ በዘርፉ ላይ ባካሄደው የዳሰሳ ጥናትና ከኅብረተሰቡ በሚቀርበው ቅሬታ መሠረት በሥራ ዕድል ፈጠራና በቴክኖሎጂ ሽግግር ላይ ክፍተት መኖሩን ገልጸዋል፡፡

ባለፉት አምስት ዓመታት ውስጥ በገቡት ውል መሠረት ያላለሙ ካስቀመጡ 23 ባለሀብቶች 6 ሺህ ሄክታር መሬት ተነጥቆ ወደ መሬት ባንክ መመለሱን በማሳያነት አቅርበዋል፡፡

ከዚህም ሰባት ባለሀብቶች ከልለው ያቆዩት 1 ሺህ 500 ሄክታር ወደ መሬት ባንክ የተመለሰው በዚህ ዓመት ነው ብለዋል፡፡

በዞኑ ኢንቨስትመንት ቦርድ ውሳኔ መሰረት ወደ ባንክ የገባው ለሌሎች ልማታዊ ባለሀብቶችና ለተደራጁ ለወጣቶች እንደሚተላለፍ ተናግረዋል፡፡

በባሌ ዞን ባለፉት ዓመታት ከ2 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር በላይ ካፒታል በማስመዘገብ የኢንቨስትመንት ፈቃድ ከወሰዱት 149 ባለሀብቶች መካከል ከ80 በመቶ የሚበልጡት በግብርና ኢንቨስትመንት የተሰማሩ ናቸው።

በዞኑ የተለያዩ አግሮ ኢኮሎጂ ሥነ-ምህዳር ያላቸው ከ12ሺህ 500 ሄክታር በላይ የኢንቨስትመንት አማራጮች እንደሚገኙ ከጽህፈት ቤቱ የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡  

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም