የኤች አይቪ ሥርጭትን ለመግታት ቫይረሱ በደማቸው የሚገኝ ወገኖች ተሳትፏቸውን እንዲያጠናክሩ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ጥሪ አቀረበ።

114

አዳማ መጋቢት 20/2011  በኢትዮጵያ የኤች.አይ.ቪ/ኤድስ ሥርጭትን ለመግታት በተከናወኑ ተግባራት የተገኙ ድሎችን ዘላቂ ለማድረግ ቫይረሱ በደማቸው የሚገኝ ወገኖች ተሳትፏቸውን እንዲያጠናክሩ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ጥሪ አቀረበ።

ኔትዎርክ ኦፍ ኔትዎርክስ ኤች.አይ.ቪ ፖዘቲቭስ ኢን ኢትዮጵያ (ኔፕ ፕላስ) 14ኛ ጠቅላላ ጉባኤው ዛሬ በአዳማ ከተማ በማካሄድ ላይ ነው።

በጉባዔው ላይ የተገኙት የጤና ጥበቃ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ሊያ ታደሰ እንደገለጹት በሃገሪቱ የኤች አይ ቪ ስርጭትን ለመከላከል በተለያዩ አካላት በተደረገ ርብርብ ከፍተኛ ለውጥ ተመዝግቧል።

በተለይ ከቫይረሱ ጋር የሚኖሩ ወገኖች በማህበር ተደራጅተው "ትውልድ ይዳን በኛ ይብቃ" በሚል መርህ አድሎና መገለል ሳይበግራቸው በፅናት መስራታቸውን አስታውሰዋል።

ይህም የበሽታው ስርጭት በሀገሪቱ በዝቅተኛ ደረጃ ላይ እንዲገኝና በበሽታው ምክንያት የሚከሰተውም የሞት መጠን እንዲቀንስ ማድረጉን ለአብነት ጠቅሰዋል።

የተገኘውን ውጤት ተከትሎ የተፈጠረው መዘናጋት ሌላ ከፍተኛ ርብርብ እንደሚጠይቅ ያስታወቁት ሚኒስትር ዴኤታዋ ለእዚህም ከቫይረሱ ጋር የሚኖሩ ወገኖች የማይተካ ሚናቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጥሪ አቅርበዋል።

ኤች.አይ.ቪን ለመከላከል እየተደረገ ላለው ጥረት የሚደረገው ዓለም አቀፍ ድጋፍ እየቀነሰ መምጣት አሳሳቢ በመሆኑ አገር በቀል የፋይናንስ አቅምን መገንባት እንደሚያስፈልግም አስታውቀዋል።

የኔትዎርክ ኦፍ ኔትዎርክስ ኤች.አይ.ቪ ፖዘቲቭስ ኢን ኢትዮጵያ (ኔፕ ፕላስ) ዳይሬክተር አቶ መኮንን አለሙ በበኩላቸው ኔፕ ፕላስ ከቫይረሱ ጋር የሚኖሩ 170 ሺህ ወገኖችን በማህበርና በጥምረት በማቀፍ የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

"በአሁኑ ወቅትም አዲስ አበባና ድሬዳዋ መስተዳድሮችን ጨምሮ በ129 ወረዳዎች ውስጥ የሕብረተሰቡን ግንዛቤ ከፍ በማድረግ የበሽታውን ስርጭት ለመግታት እየተንቀሳቀስን ነው" ብለዋል።

ባለፉት ዓመታት በተደረገው እንቅስቃሴም ከ306 ሺህ የሚበልጡ ሰዎች ፀረ ኤች.አይ.ቪ መድኃኒት እንዲጀምሩ በማድረግ ውጤት ቢገኝም ከድጋፍ እየቀነሰ  መምጣት ጋር ተያይዞ የመከላከሉ ሥራ መቀነሱን ገልጸዋል።

የኔፕ ፕላስ ቦርድ ሰብሳቢ አቶ እድላም ገብረስላሴ በበኩላቸው ኤች አይ ቪ በደማቸው የሚገኝባቸው ወገኖች የቫይረሱን ስርጭት ለመግታትና ለመቆጣጠር በተደረገ ርብርብ የከፈሉትን መስዋዕትነት አሁንም ማስቀጠል እንደሚገባ ገልጸዋል።

በተለይ ከውጭ የሚገኘው ድጋፍና ሃብት በከፍተኛ ሁኔታ እየቀነሰ በመሆኑ መንግስት፣ የግሉ ዘርፍና ባለድርሻ አካላት የሀገር ውስጥ ሀብትን በማሰባሰብ በራስ አቅም መስራት ወቅቱ የሚጠይቀው መሆኑንም አሳስበዋል።

በዓለም ጤና ድርጅት የኢትዮጵያ ካንትሪ ዳይሬክተር  ዶክተር ኢስተር ማሪይ በበኩላቸው እኤአ በ2030 ኤች አይቪ/ኤድስ የህብረተሰቡ ጤና ችግር በማይሆንበት ደረጃ ላይ ለማድረስ ግብ ተይዞ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

"ለዚህ ስኬት የኢትዮጵያ መንግስት፣ ህዝቡና ከቫይረሱ ጋር የሚኖሩ ወገኖች በሁሉም ደረጃ ወጥነትና ቀጣይነት ባለው መልኩ በሽታውን ለመከላከል የሚያደርጉትን ጥረት ድርጅቱ ይደግፋል" ብለዋል።

የበሽታው ስጋትነት እየጨመረ በመምጣቱ ስርጭቱን ለመቆጣጠር የፀረ ኤች.አይ.ቪ/ኤድስ ፕሮግራሞችን ውጤታማ ለማድረግ በትኩረት እንደሚሰራ የገለጹት ደግሞ በተባበሩት መንግስታት የኤድስ መከላከያ ድርጅት ተወካይ ዶክተር ግርማቸው ማሞ ናቸው፡፡

በሽታውን ለመከላከል በሚደረገው ጥረት ሁሉም የደርሻውን እንዲወጣም አሳስበዋል።

ለሦስት ቀናት በተዘጋጀው በዚሁ ጉባዔ ላይ ከሁሉም ክልሎች የተውጣጡ ቫይረሱ በደማቸው የሚገኙ የሕብረተሰብ ተወካዮች፣ በኤድስ ዙሪያ የሚሰሩ ድርጅቶችና ባለድርሻ አካላት በመሳተፍ ላይ ናቸው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም