በኦሮሚያ አምስት ከተሞች በአንድ ቢሊዮን ብር ወጪ መናኸሪያዎች ሊገነቡ ነው

99

አዳማ  መጋቢት 20/2011በኦሮሚያ ክልል አምስት ከተሞች በአንድ ቢሊዮን ብር ወጪ ዘመናዊ የተሽከርካሪዎች መናኽሪያዎች ግንባታ ይካሄዳል።

በከተሞቹ ግንባታው የሚካሄደው የሕዝብ ትራንስፖርት አገልግሎትን ለማዘመን በክልሉ መንግሥት በተያዘው ዕቅድ መሠረት ነው።

የኦሮሚያ ክልል ትራንስፖርት ባለሥልጣን ዋና ሥራ አስኪያጅ ረዳት ፕሮፌሰር ምህረቱ ሻንቆ መናኸሪያዎቹ ከሚገነቡ የሥራ ተቋራጮች ጋር የፊርማ ስምምነት በአዳማ ከተማ ዛሬ ተከናውኗል።ግንባታቸው በሁለት ወራት ውስጥ ይጀመራል።

ባለሥልጣኑ ደረጃውን የጠበቀና የወደፊት የከተሞቹን እድገትና የትራንስፖርት ፍሰት ባማከለ መልኩ ዲዛይኑን ማቅረቡም ተገልጿል።

በአንድ ዓመት ተኩል ጊዜ ውስጥ መናኸሪያዎቹ የሚገነባቧቸው ከተሞች አዳማ፣ሻሸመኔ፣ጅማ፣ባሌ ሮቤና ነቀምቴ ናቸው።

ዋና ሥራ አስኪያጁ በዚሁ ወቅት እንደተናገሩት መናኸሪያዎቹ የሚገነቡት የተጋልጋዩን ማህበረሰብ እርካታ ለማምጣት ነው።

ግንባታቸው ሲጠናቀቅም በትራንስፖርት ዘርፍ የሚታየውን እንግልትና መጨናነቅን እንደሚያስቀሩም እምነታቸውን ገልጸዋል።

የሥራ ተቋራጮቹ ግንባታውን በተቀመጠለት ጊዜና በጀት በማጠናቀቅ ለአገልግሎት እንዲያበቁ ዋና ሥራ አስኪያጁ አሳስበዋል።

ባለሥልጣኑም የጥራት ደረጃቸውን ጠብቀው እንዲከናወኑ በባለሙያዎች የታገዘ ክትትልና ቁጥጥር ያደርጋል ብለዋል።

ከሥራ ተቋራጮቹ መካከል አቶ አንዋር ሰዒድ እንደተናገሩት የአዳማ ከተማ መናኽሪያ ግንባታ ጥራትና ደረጃውን በጠበቀና በተቀመጠለት ጊዜ ለማጠናቀቅ መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል።

ከተማዋ በቀን ከምታስተናግደው ከ35ሺህ እስከ 40 ሺህ የሚደርሱ ተሽከርካሪዎችን ለምታስተናግደው ከተማ የሚመጥን ከተማ መናኸሪያ በጥራት ገንብተን  እናስረክባለን ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም