በእነ አቶ በረከት ጉዳይ ሲካሄድ የቆየው የጊዜ ቀጠሮ ምርመራ ተጠናቀቀ

85

ባህርዳር መጋቢት 20/2011 የጥረት ኮርፖሬት የቀድሞ ከፍተኛ አመራሮች አቶ በረከት ስምኦንና አቶ ታደሰ ካሳ ጉዳይ ሲካሄድ የቆየው የጊዜ ቀጠሮ ምርመራ ተጠናቆ መዝገቡ መዘጋቱን የባህር ዳርና አካባቢዋ ከፍተኛ ፍርድ ቤት አስታወቀ፡፡

ተጠርጣሪዎች የዋስትና ጥያቄ ማቅረብ እንደሚችሉና  በጊዜ ቀጠሮ የነበረው የምርመራ መዝገብ የተዘጋው መርማሪ ቡድኑ የማጣራት ስራውን አጠናቅቂያለሁ ብሎ በማቅረቡ እንደሆነ ችሎቱ ገልጿል፡፡

አቶ በረከት ስምኦን አሁንም ወከባና ስድቡ እንዳልቆመላቸውና ቀርቦ የሚከራከርላቸው ጠበቃ ማቅረብ አዳጋች እንደሆነባቸው ለችሎቱ አስረድተዋል፡፡

ቀደም ሲል የቀረቡት ጠበቆችም ቢሆን አሁንም ድረስእንግልት  እየደረሰባቸው መቸገራቸውን ተናግረዋል፡፡

በዚህም  ህገ መንግስታዊ መብታቸው እየተገፋ መሆኑንና ይህንን የክልሉ መንግስት እንዲያከበርላቸው ጠይቀዋል፡፡

ባለፈው ችሎቱ የተሰጠው ትዕዛዝም እየተተገበረ ባለመሆኑ አሁንም በእርሳቸውና በቤተሰቦቻቸው ላይ እየደረሰ ያለው እንግልት እንዲቆም ለችሎቱ አመልክተዋል፡፡

ጉዳዩ የሚያስከስስ እንዳልሆነና ቀደም ሲል በጋራ ሲሰራ የቆየ በመሆኑ የክስ መመስረቻ ጊዜ አጭር እንዲሆን የጠየቁት ደግሞ ሌላው ተጠርጠሪ አቶ ታደሰ ካሳ ናቸው፡፡

" አሁን ባለንበት ሁኔታ በስጋት ነው የምንኖር"  ያሉት አቶ ታደሰ ክሳችን ከባህር ዳር ውጭ ባሉ የክልሉ  ፍርድ ቤቶች እንዲታይም አመልክተዋል፡፡

ተጠርጣሪዎቹ መርማሪ ቡድኑ ምርመራውን አጠናቆ የክስ መመስረቻ ጊዜ መጠየቁ ቅሬታ እንደሌላቸው እና ሆኖም የክስ መመስረቻ ጊዜ እንዳይረዝም ጠይቀዋል፡፡

መርማሪ ቡድኑ በበኩሉ ከዳሽን ቢራ አክሲዮን ማህበር ሽያጭ ጋር በተያያዘ 635 ሰነድና 35 የባለሙያ አስተያየት ማሰባሰቡንና  ይህን አደራጅቶ በተገቢው መንገድ ክስ ለመመስረት በቂ ጊዜ ጠይቋል፡፡

የግራ ቀኙን ክርክር የተመለከተው ችሎቱ ቀደም ሲል የተሰጠው የተጠርጣሪዎችን ደህንነት እንዲጠበቅ ትዕዛዝ መጠበቅ እንዳለበት አሳስቧል፡፡

የክርክር ጉዳዩ ከባህር ዳር ከተማ ውጭ ባሉ ፍርድ ቤቶች ይታይ ለሚለው ቅሬታም በቀጣይ የሚመለከት መሆኑን አስረድቷል፡፡

"መርማሪ ቡድኑ ለክስ መመስረቻ የሚሆን ሰነድና የሰው ማስረጃ አሰባስቤ ጨርሻለሁ በማለቱ መዝገቡ ተዘግቷል" ሲል ችሎቱ አስታውቋል፡፡

ተጠርጣሪዎቹ የጊዜ ቀጠሮ መዝገቡ በመጠናቀቁ ህገ መንግስታዊ መብታቸውን ተጠቅመው ዋስትና የመጠየቅ መብት እንዳላቸው ችሎቱ ለተጠርጣሪዎቹ ገልጿል፡፡

የአማራ ክልል የስነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን አቃቢ ህግ በ15 ቀናት ጊዜ ውስጥ ሰነዱን መርምሮ ክስ እንደሚመሰርት ይጠበቃል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም