በአምስት ክልሎች የአየር ንብረት ለውጥ መቆጣጠርና መከላከል ስርዓት እየተተገበረ መሆኑ ተገለጸ

586
አዲስ አበባ ግንቦት 24/2010 በአገሪቱ አምስት ክልሎች የአካባቢና የአየር ንብረት ለውጥን ለመቆጣጠርና ለመከላከል የሚያስችል ስርዓት ተግባራዊ እየተደረገ እንደሚገኝ የአካባቢ ደንና አየር ንብረት ለውጥ ሚኒስቴር ገለጸ፡፡ በሚኒስቴሩ የብሔራዊ 'ሬድ ፕላስ ሴክረተሪያት' ፅህፈት ቤት አስተባባሪ ዶክተር ይተብቱ ሞገስ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በደን ሀብት ላይ ባሉ ፈተናዎች ምክንያት የሚከሰተውን የአካባቢና የአየር ንብረት ለውጥ ለመቆጣጠርና ለመከላከል የሚያስችል ስርዓት መተግበር ጀምሯል። ስርዓቱን ለመተግበር በቅድመ ዝግጅት ምዕራፍ በክልሎች ሰፊ ጥናት ተደርጎ የደን ፋይዳን የማስተዋወቅ ስራዎች መሰራታቸውን የጠቆሙት አስተባባሪው፤ ደን እንዳይወድምና መልሶ ማልማት በሚቻልበት መንገድ ጥናት መካሄዱን ገልጸዋል። ደንን ከውድመት መከላከልና አዲስ ደን ማልማት የካርቦን ልቀትን ለመቀነስና ከባቢ አየር ውስጥ የሚገኘውን ካርቦን በደን ውስጥ ለማከማቸት የሚያስችል ስራ መሆኑን አስረድተዋል። የደን ጥበቃና ደን መልሶ ማልማት በኦሮሚያ ክልል ቀደም ብሎ የተጀመረ ሲሆን በደቡብ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች፣ ጋምቤላ፣ አማራና ትግራይ ክልሎች በተመሳሳይ ወደ ስራ መገባቱን ጠቅሰዋል፡፡ የኦሮሚያ ክልል ቀደም ብሎ በመጀመሩ የችግኝ ልማቱን አከናውነው የመትከያ ቦታ መረጣ ላይ እንደሆኑም ተጠቅሷል፡፡ ለፕሮጀክቱ ማስፈጸሚያ ከኖርዌይ መንግስት 80 ሚሊዮን ዶላር እንዲሁም ከአለም ባንክ 18 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ መገኘቱን ዶክተር ይተብቱ ተናግረዋል፡፡ ፕሮጀክቱ በክልሎቹ የሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎች የደን ሀብታቸውን እየጠበቁና እያለሙ ተጠቃሚ የሚሆኑበትን ስርዓት በጥምረት ያስኬዳል ያሉት አስተባባሪው፤ በዚህም ከ120ሺህ በላይ ዜጎች ተጠቃሚ እንደሚሆኑ ገልጸዋል። በክልሎቹ የሚገኙት የህብረተሰብ ክፍሎች የደን ጥበቃና ልማቱን በማህበር ተደራጅተው እንዲያከናውኑት እንደሚደረግ ተገልጿል፡፡ የደን ልማትና ጥበቃ የሚያከናውኑት ዜጎች ጎን ለጎን ቡና እና ማር ልማት ላይ እንዲሰማሩ፤ እንዲሁም በግብርናው ዘርፍ የምርጥ ዘር ድጋፍና በግብርና ምርት ማቀነባበር በስፋት ተሰማርተው ተጠቃሚ እንዲሆኑ የሚደረግ መሆኑን ዶክተር ይተብቱ አስረድተዋል። እ.ኤ.አ 2022 ድረስ የሚቆየው ፕሮጀክቱ ወደ 880 ሺህ ሄክታር አዲስ ደን፤ እንዲሁም በደን መልሶ ማዳን ተግባር ወደ 660ሺህ ሄክታር እንደሚፈጠር አስተባባሪው ጠቁመዋል፡፡ ቀጣይም በሌሎች ክልሎች ፕሮጀክቱን ተደራሽ ለማድረግ ድጋፍ የሚገኝበትን መንገድ በማመቻቸት የማስፋፋት ስራዎች እንደሚከናወኑ ዶክተር ይተብቱ ተናግረዋል፡፡ ፕሮጀክቶቹ ውጤታማ እንዲሆኑ የዘርፉን ባለሙያዎች ክልሎች ወረዳዎች ድረስ ተደራሽ እንዲያደርጉና አስፈላጊ የሆኑ ቁሳቁሶችን ማሟላት ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም