የቦረና ሳይንት ወረሂመኑ ብሄራዊ ፓርክን ደህንነት ለማስጠበቅ እየተሰራ ነው

97

ደሴ መጋቢት 20/2011 የቦረና ሳይንት ወረሂመኑ ብሄራዊ ፓርክ ይዞታን በማስፋፋት  ደህንነቱ ተጠብቆ ለጎብኚዎች መዳረሻ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን የፓርኩ ጽህፈት ቤት አስታወቀ፡፡

የጽህፈት ቤቱ ኃላፊ አቶ አንተነህ ተስፋዬ እንደገለጹት ፓርኩ ከ2002 ዓ.ም.  ሲከለል "ቦረና ሳይንት" በሚል ስያሜ 4 ሺህ 375 ሄክታር መሬት ሸፍኖ የተከለለ ነበር፡፡

በተያዘው ወር መግቢያ አካባቢ 10 ሺህ ሄክታር ተጨምሮለት በማስፋፋት "ቦረና ሳይንት ወረሂመኑ" ብሄራዊ ፓርክ የሚል ስያሜ  ተሰጥቶታል፡፡

ህብረተሰቡ እንስሳቱን  ወደ ፓርኩ እንዳያስገባ ፣ ደንን አለአግባብ እንዳይመንጠርና ከሰል እንዳይከሰል በማድረግ ከጥፋት ለመታደግ ከባላድርሻ አካላት ጋር  መሰራት ተጀምሯል፡፡

 አቶ አንተነህ "በፓርኩ ውስጥ የሚገኙትን ቀይ ቀበሮ፡ ጭላዳ ዝንጀሮና ሌሎች የዱር እንስሳትና ብዛት ያላቸው የአእዋፍ ዝርያዎችን የመጠበቅ ስራም ይሰራል "ብለዋል፡፡

ፓርኩ ለጎብኝዎች ምቹ እንዲሆንም ከመካነሰላም ከተማ ፓርኩ ድረስ ያለውን 18 ኪሎ ሜትር መንገድም የማስተካከል ስራ እየተከናወነ እንደሚገኝ አመልክተዋል፡፡

እንዲሁም ስድስት  የጥበቃና የእንግዳ ማረፊያ ካምፖች ተሰርተው በጸሀይ ኃይል የሚሰራ  መብራትና ውሃ እንደገባላቸው ጠቅሰው "ቀሪ የሎጅና የውሃ አቅርቦትም ይሟላል "ብለዋል፡፡

የፓርኩ ጽህፈት ቤት ግንባታ ሶስት ሚሊዮን 600ሺህ ብር በሆነ ወጪ  ተጠናቆ ስራ ጀምሯል፡፡

ኃላፊው እንዳሉት ፓርኩ ከሚያዋስናቸዉ ቦረና፣ አማራ ሳይንት፣መሃል ሳይንት፣ ተንታ፣ ለጋምቦና መቅደላ ወረዳዎች አመራሮችና ህብረተሰቡ ጋር በመወያየት በውስጡ ያሉ ተሳቢ፣ አጥቢና አእዋፋትን በመቁጠር ትክክለኛ መረጃ ለመያዝ እየተሰራ ነው፡፡

የአማራ ሳይንት ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ መርጊያው  ደሳለው በበኩላቸው በየደረጃው ከመንግስት፤ የህብረተሰብ መሪዎች ፣ የሀገር ሽማግሌዎችና የኃይማኖት አባቶች ጋር በመቀናጀት በሚያዋስኗቸው አስር  ቀበሌዎች ፓርኩን ለመንከባከብ ጥረት አንደሚያደርጉ ተናግረዋል፡፡

"ፓርኩ የሀገር ሀብት በመሆኑ ከስጋት በማዳን ከማንኛውም ጥቃት ለመከላከል ተባብረን እንሰራለን" ብለዋል ።

ግጦሽ ፍለጋ ወደ ፓርኩ እንስሳት የሚነዱም ሆነ ተፅእኖ በሚፈጥሩ ሰዎች  ላይ የማስተካከያ እርምጃ በመውሰድ ኃላፊነታቸውን ለመወጣት ዘግጁ መሆናቸውን አመልክተዋል፡፡

" ፓርኩን በመንከባከብ የቱሪስት መዳረሻ እንዲሆን ህብረተሰቡን አስተባብረን እንሰራለን"  ያሉት ደግሞ የመቅደላ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ ተፈራ ሞላ ናቸው፡፡

አዲስ የተከለሉ ቦታዎችንም ለህብረተሰቡ ግልጽ በማድረግ ከግጦሽ፣ ከደን ጭፍጨፋና ከሰል ከማክሰል እንዲቆጠቡ ግንዛቤ የመፍጠር ስራ እያካሄዱ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

የቦረና ሳይንት ወረሂመኑ ብሄራዊ ፓርክ በውስጡ 17 አጥቢ የዱር እንስሳት ዝሪያዎች ፣ በኢትዮጵያ ብቻ የሚገኙ ቀይ ቀበሮ፣ ጭላዳ ዝንጀሮና ብርቅዬ የአእዋፍ ዝርያዎች እንደሚገኙ የፓርኩ ጽህፈት ቤት አመልክቷል፡፡

 ይገኛሉ፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም