አሲዳማ የእርሻ መሬትን በኖራ በማከም ምርታማ ማድረጋቸውን አርሶ አደሮች ገለጹ

58

ጎንደር መጋቢት 20//2011 አሲዳማ የእርሻ መሬትን በኖራ በማከም ምርታማ እንዲሆን ማድረጋቸውን የማዕከላዊ ጎንደር ዞን አርሶ አደሮች ተናገሩ።

የዞኑ ግብርና መምሪያ በመኸር ወቅት 250 ሄክታር አሲዳማ የእርሻ መሬት ምርታማነትን እያሳደግኩ   ነው ብሏል።

የዞኑ አንዳንድ አርሶ አደሮች ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንደገለጹት ምርት መስጠት አቁሞ የነበረ አሲዳማ የእርሻ መሬትን በኖራ በማከም ምርታማ እንዲሆን በማድረግ ላይ ናቸው።

በወገራ ወረዳ የብራ ቀበሌ ነዋሪው አርሶ አደር ክፍሌ አይቸው በ2010/11 የምርት ዘመን የኖራ አፈር ቴክኖሎጂን በመጠቀም በግማሽ ሄክታር ማሳ ላይ ባለሙት ስንዴ ከቀድሞው በስድስት ኩንታል ብልጫ ያለው ምርት ማግኘታቸውን ተናግረዋል።

የዚሁ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ምትኩ ባዬ በበኩላቸው በግብርና ባለሙያዎች ድጋፍ አሲዳማ መሬታቸውን በኖራ በማከም ወደ ምርት ማስገባታቸውን ገልጸዋል።

በግማሽ ሄክታር መሬት ላይ 15 ኩንታል ኖራ በመጠቀም ለግጦሽ ሳር አውለውት በነበረው መሬት አራት ኩንታል ባቄላ አምርተው 12 ሺህ ብር ማግኘታቸውን አሰረድተዋል።

የጣቁሳ ወረዳ ነዋሪው አርሶ አደር ሲሳይ መንግስቴ በበኩላቸው ባለፈው ዓመት 10 ኩንታል ኖራ በመጠቀም በግማሽ ሄክታር መሬት ላይ የዘሩት ዳጉሳ ምርታማነት ከአምስት ወደ ሰባት ኩንታል ማደጉን አስታውቀዋል።

የዞኑ ግብርና መምሪያ የአፈር ለምነት ባለሙያ ወይዘሮ ደባካ አለሙ በዚህ ዓመት በ1 ሺህ 637 የእርሻ መሬት ላይ የአፈር ናሙና መሰባሰቡን ገልጸው፣ በጎንደር አፈር ምርመራ ላቦራቶሪ በተደረገው ፍተሻ 366 ናሙናዎች አሲዳማ ይዘት እንዳላቸው ተረጋግጧል ብለዋል።

በዚህ ምርት ዘመን በአለፋ ጣቁሳና በወገራ ወረዳዎች 850 የሚገኙ አርሶ አደሮችን በማሰልጠንና 250 ሄክታር አሲዳማ መሬትን አክሞ ወደ ሰብል ልማት ለማስገባት ዝግጅት እየተደረገ መሆኑንም አስታውቀዋል።

በምርት ዘመኑ 5 ሺህ ኩንታል የኖራ አፈር ለአርሶ አደሮቹ እንደሚሰራጭ ባለሙያዋ ገልጸዋል፡፡

የጎንደር የአፈር ምርመራ ላቦራቶሪ ኃላፊ አቶ ታደሰ ደምሴ በበኩላቸው በሰሜን፣ በደቡብ፣ በምዕራብና ማዕከላዊ ጎንደር ዞኖች ከ4 ሺህ በላይ የአፈር ናሙናዎችን በላቦራቶሪ መለየታቸውን ገልጸዋል።

ባቄላ፣ አተር፣ ገብስና ስንዴ ሰብሎች አሲዳማ አፈርን ተቋቁመው በቂ ምርት የመስጠት አቅም የላቸውም ያሉት ኃላፊው፣ መሬቱን በኖራ ማከም አማራጭ ቴክኖሎጂ ሆኖ መገኘቱን ተናግረዋል፡፡

በማዕከላዊ ጎንደር ዞን ስምንት ወረዳዎች ለአሲዳማነት የተጋለጠ የእርሻ መሬት አለ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም