በጎንደር ከተማ በሕብረተሰቡ ተሳትፎ 70 ሚሊዮን ብር የመሰረተ ልማት ሥራዎች እየተከናወኑ መሆናቸው ተጠቆመ

66

ጎንደር መጋቢት 20/2011 በጎንደር ከተማ በሕብረተሰቡ ተሳትፎ  70 ሚሊዮን ብር የመሰረተ ልማት ሥራዎች እየተከናወኑ መሆናቸው ተጠቆመ፡፡

በጎንደር ከተማ ከ365 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ የተለያዩ የመሰረተ ልማት ማስፋፊያ ሥራዎች በመከናወን ላይ መሆናቸውን የከተማው ቤቶችና ኮንስትራክሽን ልማት መምሪያ አስታወቀ፡፡

በመምሪያው የከተሞች ተቋማዊና መሰረተ ልማት እድገት ፕሮግራም አስተባባሪ አቶ ታምራት ልዑልሰገድ ለኢዜአ እንዳስታወቁት በከተማዋ በዓለም ባንክና በመንግስት መደበኛ በጀት ለመሰረት ልማት ሥራዎቹ ከ365 ሚሊዮን ብር በላይ ተመድቧል።

በተመደበው በጀትና በህብረተሰቡ ድጋፍ እየተከናወኑ ካሉ ሥራዎች ማካከልም 12 ነጥብ 8 ኪሎ ሜትር የጌጠኛ ድንጋይ ንጣፍ መንገድ፣ አራት ኪሎ ሜትር የጠጠር መንገድ ግንባታ፣ 5 ነጥብ 6 ኪሎ ሜትር የውሃ የማፋሰሻ ቦይና 12 ኪሎ ሜትር የውሃና የኤሌክትሪክ መስመር ዝርጋታ ይገኙበታል፡፡

በመምሪያው የከተሞች ተቋማዊና መሰረተ ልማት እድገት ፕሮግራም አስተባባሪ አቶ ታምራት ልዑልሰገድ ለኢዜአ እንዳሉት ህብረተሰቡ በባለቤትነት በመሳተፍ ለመሰረተ ልማት ሥራዎች ድጋፍ እያደረገ ይገኛል፡፡

ህብረተሰቡ በገንዘብ፣ በቁሳቁስና በጉልበት 128 ሚሊዮን ብር በበጀት ዓመቱ አስተዋጽኦ እንዲያደርግ ታቅዶ እየተሰራ ሲሆን እስካሁንም ከግማሽ በላይ አስተዋጽኦ ማድረጉን ጠቁመዋል፡፡

የመሰረተ ልማት ዝርጋታ ሥራዎቹ እስከ በጀት ዓመቱ መጨረሻ የሚጠናቀቁ ሲሆን የሕብረተሰቡ ድጋፍም ተጠናከሮ እንዲቀጥል ጥረት እየተደረገ ነው፡፡

እንደአቶ ታምራት ገለጻ እየተሰሩ ባሉ የመሰረተ ልማት ሥራዎች ከ2 ሺህ 600 በላይ ለሆኑ ዜጎች የሥራ ዕድል ተፈጥሯል፡፡

በከተማው የማራኪ ክፍለ ከተማ ነዋሪ አቶ ክፍሌ እጃርገው በበኩላቸው " የልማት ሥራዎቹ ባለቤት በመሆናችን በጥራትና በጊዜ እንዲጠናቀቁ እንዲሰሩ ክትትል ከማድረግ ባለፈ 2 ሺህ ብር ድጋፍ አድርጊያለሁ" ብለዋል፡፡

የጌጠኛ ድንጋይ ንጣፍ መንገድ ከዚህ ቀደም በአካባቢያቸው ባይሰራም ዘንድሮ በመጀመሩ ደስተኛ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

" የጠጠር መንገዱ ክረምቱ ሳይገባ ተጠናቆ ለትራፊክ ክፍት መሆን ይኖርበታል"  ያሉት ነዋሪው  በተለይ "ሕዳሴ ሰፍር" ተብሎ የሚጠራው አካባቢ በክረምት ወራት አስቸጋሪ በመሆኑ ከወዲሁ ትኩረት እንዲሰጠው አመልክተዋል፡፡

" በሚሰሩ መሰረተ ልማት ሥራዎች በገንዘብና በጉልበት በመሳተፌ ልማቱ የእኔነት ስሜት አሳድሮብኛል" ያሉት ደግሞ በከተማው የዞብል ክፍለ ከተማ ነዋሪ አቶ ጎሸ ከልካይ ናቸው፡፡

ልማቱ በአግባቡ እንዲከናወን ከመከታተል ባለፈ ጉዳት እንዳይደርሰበት የመጠበቅ ኃላፊነት በአግባቡ እንደሚወጡም አረጋግጠዋል፡፡

በክረምት ወራት በቤታቸው ጎርፍ እየገባ ጉዳት እያደረሰባቸው መሆኑን የተናገሩት ደግሞ የፋሲል ክፍለ ከተማ ነዋሪ ወይዘሮ ሀብታም አያናው ናቸው፡፡

የጎርፍ መከላከያው እንዲሰራ ተደጋጋሚ ጥያቄ ሲያቀርቡ መቆየታቸውን አስታውሰው በአሁኑ ወቅት ቅሬታቸው ሰሚ አግኝቶ የጎርፍ መከላከያ ግንባታ ሥራ በአካባቢያቸው መጀመሩ እንዳስደሰታቸው ተናግረዋል፡፡

የሥራ ዕድል ከተፈጠረላቸው መካከል ወጣት ተፈራ ጌጡ በበኩሉ በአነስተኛ ድልድይ ግንባታ ሥራዎች በግንበኝነት ሙያ ተቀጥሮ በቀን 200 ብር እየተከፈለው መሆኑን ገልጿል፡፡

በከተማዋ እየተከናወኑ ያሉት የመሰረተ ልማት ሥራዎች ሙሉ በሙሉ ተጠናቀው ለአገልግሎት ሲበቁ የከተማዋን የመሰረተ ልማት ሽፋን አሁን ካለበት 88 ከመቶ ወደ 94 በመቶ እንደሚያሳድገው ለማወቅ ተችሏለ ፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም