የጎንደር ከተማን የውሃ አቅርቦት ለማሻሻል በ17 ሚሊዮን ብር ጥልቅ ጉድጓዶች እየተቆፈሩ ነው

95

ጎንደር መጋቢት 20/2011 የጎንደር ከተማን የንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት ለማሻሻል በ17 ሚሊዮን ብር ወጪ የሁለት ጥልቅ ጉድጓዶች ቁፋሮ ሥራ እየተካሄደ መሆኑን የከተማው መጠጥ ውሃና ፍሳሽ አገልግሎት ጽህፈት ቤት አስታወቀ፡፡

የጽህፈት ቤቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ሃይማኖት በለጠ ለኢትዮዽያ ዜና አገልግሎት እንደገለጹት  በከተማው የሚታየውን የንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት ችግር ለመፍታት እያንዳንዳቸው 400 ሜትር ጥልቀት ያላቸው ሁለት የውሃ ጉድጓዶች ቁፋሮ ሥራ እየተካሄደ ነው።

በምስራቅ ደንቢያ ቢትና ጉራምባ ተብሎ በሚጠሩት አካባቢዎች እየተቆፈሩ ያሉት ጉድጓዶች ወጪያቸው ከክልሉ መንግስት በተገኘ የገንዘብ ድጋፍ የሚሸፈን ነው።

የአንደኛው ጥልቅ የውሃ ጉድጓድ ቁፋሮ ሥራ መጠናቀቁን ያስታወቁት ሥራ አስኪያጁ የሁለተኛው የጉድጓድ ቁፋሮ ስራም ከ50 በመቶ በላይ መድረሱን አመልክተዋል።

አቶ ሃይማኖት እንዳሉት የውሃ ጉድጓዶቹን በዚህ ዓመት ሙሉ በሙሉ በማጠናቀቅ በቀጣዩ ዓመት ወደ ዋናው የውሃ ስርጭት ስርዓት ለማስገባት ታቅዷል፡፡

የውሃ ጉድጓዶቹ በቀን 5 ሺህ ሜትር ኪዩብ ውሃ የማመንጨት አቅም የሚኖራቸው ሲሆን ተጨማሪ ሦስት ጥልቅ የውሃ ጉድጓዶች ቁፋሮ ስራም በቀጣዩ ዓመት እንደሚጀመር ተናግረዋል።

በአሁኑ ወቅት ለጎንደር ከተማ ህዝብ ከአንገረብ የመጠጥ ውሃ ግድብና ቆላድባ ከሚገኙ ስምንት ጥልቅ ጉድጓዶች በቀን 14 ሺህ ሜትር ኪዩብ ውሃ እየቀረበ መሆኑን ገልጸዋል።

በአሁኑ ወቅት ለሕብረተሰቡ እየቀረበ ያለው የንጹህ መጠጥ ውሃ የከተማውን የውሃ ፍላጎት 40 በመቶ ብቻ የሚሸፍን ነው።

የገጠመውን የውሃ እጥረት ተከትሎ ካለፈው የካቲት ወር 2011 ዓ.ም ጀምሮ የፈረቃ ውሃ ስርጭት መጀመሩን አቶ ሃይማኖት አመልክተዋል።

"የነዋሪዎች ቁጥር መጨመር፣ የግንባታ ሥራዎች መስፋፋትና የፋብሪካዎች መበራከት የከተማውን የውሃ አቅርቦት ፍላጎት እንዲጨምር አድርጎታል" ብለዋል።

የጎንደር ከተማ ነዋሪ አቶ ታደሰ አይናለም በበኩላቸው በተለይ በበጋ ወቅት በንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት እጥረት እንደሚቸገሩ ተናግረዋል።

የንጹህ መጠጥ ውሃውን እጥረት ችግር በመፍታት በኩል የከተማው የውሃ ጽህፈት ቤት በትኩረት እንዲሰራ ጠይቀዋል።

" በከተማው ዳርቻ ለሚገኙ መኖሪያ ቤቶች የንጹህ መጠጥ ውሃ በፍትሃዊነት እየደረሰ አይደለም፤ ስርጭቱም ፍትሃዊ ሊሆን ይገባል" ያሉት ደግሞ የከተማው ነዋሪ ወይዘሮ እቴናት መንግስቱ ናቸው፡፡

የመገጭ ሰራባ መስኖ ፕሮጀክት ሲጠናቀቅ በዓመት 31 ነጥብ 5 ሚሊዮን ሜትር ኪዩብ ውሃ ለከተማው ለማቅረብ የሚያስችል ጥናት በመካሄድ ላይ እንደሚገኝ ከጽህፈት ቤቱ የተገኘ መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም