በዓለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮና ኢትዮጵያን ጨምሮ ከ67 አገራት የተወጣጡ አትሌቶች ይካፈላሉ

66

አዲስ አበባ መጋቢት 20/2011 በዴንማርክ አርሁስ ከተማ ነገ በሚካሄደው 43ኛው የዓለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮና ኢትዮጵያን ጨምሮ ከ67 አገራት የተወጣጡ 582 አትሌቶች ይካፈላሉ።

ውድድሮቹ በአዋቂ ወንዶችና ሴቶች የ10 ኪሎ ሜትር፣ በወጣት ወንዶች 8 ኪሎ ሜትር፣ በወጣት ሴት 6 ኪሎ ሜትርና በ8 ኪሎ ሜትር ድብልቅ የዱላ ቅብብል የሚካሄዱ ሲሆን ኢትዮጵያ በሁሉም ርቀቶች ላይ ትካፈላለች።

ውድድሮቹ ነገ ከቀኑ ስድስት ሰአት ጀምሮ የሚካሄዱ ይሆናል።

28 አትሌቶችን ጨምሮ 46 ልዑካን ቡድን የያዘው የኢትዮጵያ ልዑክ ውድድሩ ወደ ሚካሄድበት ስፍራ መጋቢት 17 ቀን 2011 ዓ.ም  ማቅናቱ የሚታወስ ነው።

ትናንት የልዑካን ቡድኑ አርሁስ ከተማ የደረሰ ሲሆን አትሌቶቹም ውድድሩ በሚካሄድበት ስፍራ በሚገኝ ቦታ ቀለል ያለ ልምምድ ማድረጋቸውን የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን አስታውቋል።

የልዑካን ቡድኑን የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌደሬሽን ጊዜያዊ ፕሬዚዳንት ኮሎኔል ደራርቱ ቱሉ የሚመራ ሲሆን አቶ ዱቤ ጅሎ ደግሞ የቴክኒክ ቡድን መሪ ናቸው።

ሶስት የህክምና ቡድን አባላት፣ ዘጠኝ አሰልጣኞችና የፌዴሬሽን የስራ አስፈጻሚዎች ኮሚቴ አባላትም በልዑካን ቡድኑ ውስጥ ተካተዋል።

በዚህ ውድድር የሚካፈሉት አትሌቶች የካቲት 3 ቀን 2011 ዓ.ም በተካሄደው የጃንሜዳ ኢንተርናሽል አገር አቋራጭ ውድድር የተመረጡ ናቸው።

የተመረጡት አትሌቶች ከየካቲት 6 ቀን 2011 ዓ.ም ጀምሮ በአዲስ አበባ አራራት ሆቴል ተቀምጠው ልምምዳቸውን ሲሰሩ መቆየታቸው ይታወቃል።

ነገ በሚካሄዱት ሁሉም ውድድሮች የኢትዮጵያና የኬንያ አትሌቶች የቅድሚያ የማሸነፍ ግምቱን ያገኙ ሲሆን በአዋቂ ወንዶችና ሴቶች የ10 ኪሎ ሜትር የሚካሄዱት ውድድሮች ከወዲሁ የአትሌቲክሱን ማህበረሰብ ትኩረትን ስቧል።

በአዋቂ ወንዶች የ10 ኪሎ ሜትር ውድድር አትሌት ሰለሞን ባረጋና ኬንያዊው አትሌት ጂኦፍሬይ ካምዎሮር በአዋቂ ሴቶች አትሌት ለተሰንበት ግደይና ኬንያዊቷ አትሌት ሄለን ኦቢሪ የሚያደርጉት ፉክክር ተጠባቂ ሆኗል።

በአጠቃላይ ለነገው ውድድር የዓለም አቀፉ የአትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማህበር 310 ሺህ ዶላር ሽልማት አዘጋጅቷል።

ኢትዮጵያ ከሁለት ዓመት በፊት በዩጋንዳ ርዕሰ መዲና ካምፓላ በተካሄደው 42ኛው የዓለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮና በ4 የወርቅ፣በ4 የብርና በ1 የነሐስ በድምሩ ዘጠኝ ሜዳሊያዎችን በማግኘት ሁለተኛ ደረጃን ይዛ ማጠናቀቋ የሚታወስ ነው።

ኬንያ በሻምፒዮናው 4 የወርቅ፣5 የብርና 3 የነሐስ ሜዳሊያ በድምሩ 12 ሜዳሊያዎችን በመሰብሰብ አሸናፊ መሆኗ አይዘነጋም።

የዓለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮና ከ1965 ዓ.ም ጀምሮ በተለያዩ ሀገራት እየተካሄደ የሚገኝ ውድድር ሲሆን ኢትዮጵያ ደግሞ ከ1973 ዓ.ም ጀምሮ በዚህ ሻምፒዮና እየተካፈለች ትገኛለች።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም