ስድስት አገር በቀል ምርቶች ደረጃ ሊወጣላቸው ነው

403

አዲስ አበባ መጋቢት 20/2011 የኢትዮጵያ ደረጃዎች ኤጀንሲ ለስድስት አገር በቀል ምርቶች ደረጃ ለመስጠት የመጨረሻው ምዕራፍ ላይ መሆኑን ገለጸ።

ደረጃ እየተዘጋጀላቸው ያሉ ምርቶች በርበሬ፣ ሽሮ፣ ጠጅ፣ በሶ፣ቆሎና ለወጥ ማጣፈጫ የሚውሉ ቅመማቅመሞች ናቸው።

በኢትዮጵያ ደረጃዎች ኤጀንሲ የደረጃ ዝግጅት ዳይሬክተር አቶ ይልማ መንግስቱ ለኢዜአ እንዳሉት ለነዚህ አገር በቀል ምርቶች ደረጃ ለማውጣት የሰነድ ዝግጅት፣ውይይትና በላብራቶሪ ለማረጋገጥ ረዥም ጊዜ ወስዷል።

እንደ ዳሬክተሩ ገለጻ ደረጃውን በተዘጋጀው መነሻ ሰነዱ ላይ ከሚመለከታቸው ጋር ውይይት ተደርጎ በላብራቶሪ የማረጋገጥ ደረጃ ላይ ነው።

እነዚህ ምርቶች በአገር ውስጥ በስፋት ጥቅም ላይ ከሚውሉ ምርቶች መካከል ከመሆናቸው በተጨማሪ ወደ ተለያዩ የዓለም አገራት እየተላኩ ይገኛሉ።

ለአብነትም ጠጅ የሚልኩ ኢትዮጵያውያን የተቀባይ አገራት ዜጎች በውስጡ ያለውን የአልኮል መጠን፣ የሚይዛቸውን ንጥረ ነገሮችና ለጤና ተስማሚነታቸው ላይ ማረጋገጫ ይጠይቃሉ።

በተጨማሪም ከኢትዮጵያ ባህላዊ ምግቦች ዶሮ ወጥን ጨምሮ ሌሎች ምግቦች ወደ ውጭ እየተላኩ ሲሆን በውስጣቸው ስላለው ይዘት ማረጋገጥ ያስፈልጋል ብለዋል።

ዳይሬክተሩ እንደተናገሩት ደረጃ መውጣቱ እነዚህን ጥያቄዎች ለመመለስና የአገር ገጽታን ለማስተዋወቅ ይጠቅማል።

በአገር ውሰጥም በተለምዶ በሽሮ፣ ጠጅና ሌሎች የታወቁ አካባቢዎች የሚጠቀሱ ሲሆን በዘመናዊ መንገድ በላብራቶሪ በመፈተሽ ትክክለኛ ደረጃቸው ይቀመጥላቸዋል።

ደረጃውን ለመስጠት ምርቶቹ በውስጣቸው ያለውን ትክክለኛ ይዘት ለማረጋገጥ የመጨረሻው ምዕራፍ እውቅና ባላቸው ላብራቶሪዎች ፍተሻ እየተደረገ ነውም ብለዋል።

በኢትዮጵያ በተለያየ ጊዜ ከበርበሬና ሌሎች ለምግብነት ከሚውሉ ምርቶች ጋር አልፎ አልፎ በዓድ ነገሮችን ሲቀላቀሉ ይስተዋላል ያሉት ዳይሬክተሩ በሚወጣው ደረጃ ንጹህ በርበሬ ምን ደረጃዎችን ማሟላት እንዳለበትና በዓድ ነገረ ተጨመረ የሚባለው ምን ሲሆን ነው የሚለውን ለመለየት እንደሚረዳ አስረድተዋል።

ደረጃውን ለማውጣት ከዓለም ባንክ ለሌሎች የደረጃ ተግባራት ጭምር ከተገኘ 50 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል።

በአሁኑ ወቅትም የላብራቶሪ ፍተሻ ውጤቶች እየተጠበቁ ሲሆን ውጤቱ ሲጠናቀቅ ይፋ ይሆናል ብለዋል።

እነዚህ አገር በቀል ምርቶች መነሻ ሰነድና የጥራት መስፈርት ኖሯቸው በቀጣይ እያደጉ የሚሄዱና የኢትዮጵያ ምርት የሚተዋወቅበት እንዲሁም የህበረተሰቡን ጤና ለመጠበቅ ዋስትና የሚሰጥበት ነው።