አምባሳደር አያሌው ጎበዜ ከጆርጂያ ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጋር ተወያዩ

177
አዲስ አበባ ግንቦት 24/2010 በቱርክ የኢትዮጵያ ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር አያሌው ጎበዜ ከጆርጂያው ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴቪድ ዶንዱአ ጋር ተወያዩ። አምባሳደር አያሌው በውይይታቸው ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀንድ ሰላም በማስከበር ዙሪያ ከፍተኛ ሚና እንዳላት ገልጸው፣ በመገንባት ላይ ያለው የታላቁ የህዳሴ ግድብ ለአገሪቱ ከፍተኛ ጥቅም ከማስገኘት በተጨማሪ ለታችኛው ተፋሰስ አገሮች ያለውን ጠቀሜታ መግለጻቸውን ከውጭ ጉዳይ ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት የተገኘው መረጃ ያመለክታል። በሁለቱ አገራት መካከል ያለው ግንኙነት የበለጠ እንዲጠናከር በየወቅቱ ምክክሮች እንዲደረጉ የአገራቸውን ፍላጎት የጆርጂያው ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴቪድ ዶንዱአ ጠቅሰዋል። በተመሳሳይ አምባሳደር አያሌው ከጆርጂያው የባህል ምክትል ሚኒስትር ክቡር ሌቫን ካራቲሽቪሊ ጋር ተወያይተዋል። ጆርጂያ የብዙ ባህል ቅርስ መገኛ እንደሆነችና በዩኔስኮ የማይዳሰስ ቅርስ ለማስመዝገብ በተደረገው ጥረት ኢትዮጵያ ላደረገችው ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል። አምባሳደር አያሌው ጎበዜ መቀመጫቸውን ቱርክ በማድረግ በጆርጂያም የኢትዮጵያ ተጠሪ ይሆናሉ። ኢትዮጵያና ጆርጂያ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸውን የጀመሩት እንደ አውሮጳውያን አቆጣጠር በ1993 ነው።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም