በሀገሪቱ ተግዳሮትን ለመሻገር መልካም ስብዕና ያላቸው ወጣት አመራሮች ማፍራት እንደሚያስፈለግ ተገለጸ

87

አዳማ መጋቢት 19/2011 በሀገሪቱ እያጋጠመ ያለውን ተግዳሮት ለመሻገር  በየደረጃው  መልካም ስብዕና ያላቸው  ወጣት አመራሮችን ማፍራት እንደሚያስፈልግ የሴቶች ፣ህፃናትና ወጣቶች ሚኒስትር  ወይዘሮ ያለም ፀጋይ ገለጹ።

ከሁሉም ክልሎችና ሁለቱ የከተማ አስተዳደሮች  ለተውጣጡ ተተኪ አመራሮች ባለፉት አስር ቀናት በቢሾፍቱ  ከተማ ሲሰጥ የቆየው ስልጠና ዛሬ ተጠናቋል።

በስልጠናው ማብቂያ  የተገኙት ሚኒስትሯ ወይዘሮ ያለም ፀጋይ እንዳሉት  በሀገሪቱ   መልካም ስብዕና ያላቸው ወጣት አመራሮች መገንባት ያስፈልጋል፡፡

ይህም በምክንያት የሚቃወምና የሚደግፍ  ወጣት ኃይል በብዛት በማፍራት ሀገሪቱና ህዝቦቿ አሁን ካጋጠማቸው  ተግዳሮት ማሸጋገር እንደሚቻል ገልጸዋል፡፡

የስልጠናው ተካፋይ ወጣት አመራሮች ኃላፊነታቸውን በተገቢው በመወጣት ለሀገሪቱ እድገትና ብልጽግና ሊረባረቡ እንደሚገባ አሳስበዋል።

" ሀገሪቱ የወጣቱን አቅምና ችሎታ በአግባቡ አልተጠቀመችበትም " ያሉት ሚኒስትሯ ይህንን ክፍተት ለመሙላት ታስቦ ስልጠናው መዘጋጀቱን አስታውቀዋል።

አቅም ፣ ችሎታና ክህሎት እንዲሁም ኃላፊነት የሚሰማው ወጣት አመራር መፍጠር ጊዜ የሚሰጠው ጉዳይ እንደልሆነ ገልጸው የስልጠናው ዓላማም እራሱን የቀየረ ለለውጥ የሚተጋ የተሻለ አመራር ለማብቃት መሆኑን አስረድተዋል።

ከስልጠናው ተሳታፊዎች መካከል ከቤንሻጉል ክልል የአሶሳ ወረዳ ወጣቶች ማህበር ኃሃፊ አሚና አሲዳቅ በሰጠችው አስተያየት ስልጠናው የአመራር ክህሎትን በማበልጸግ  የተሻለ ለመስራት መነቃቃት ፈጥሮልኛል " ብላለች።

ወጣቷ እንዳለችው ከስልጠናው በተለይም ተግባቦትን በማዳበር  የህዝብ ለህዝብ ግንኙነትን ለማበልጸግ የሚረዳ አቅም አግኝታለች፡፡

የአፋር ብሄራዊ ዴሞክራሲ ፓርቲ ወጣቶች ሊግ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል መሀመድ አደም በበኩሉ ከብሄረተኝነት በመላቀቅ ለሀገር አንድነት፣ ሰላም፣ ልማትና እድገት በጋራ   መስራት እንደሚቻል ከስልጠናው ግንዛቤ ማግኘቱን ተናግራል።

ወደ አካባቢው ሲመለስም በማህበራዊ ሚዲያ የሚነዛውን የጥላቻ ፕሮፖጋንዳ በተሻለ የሀሳብ ልዕልና በመርታት የክልሉ ወጣቶች በሁሉም መስክ ተሳትፏቸውን እንዲያጠናክሩ በትኩረት እንደሚሰራም ገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም