የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት የትራፊክ አደጋ ደረሰባቸው

90

አዲስ አበባ መጋቢት 19/2011 የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ዛሬ ጠዋት የተፈናቀሉ ወገኖችን ለመጎብኘት ወደ መስክ ሲወጡ የትራፊክ አደጋ ደረሰባቸው።

በአሁኑ ወቅት በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል የህክምና እርዳታ እየተደረገላቸው ይገኛል።

የምክር ቤቱ አባላት በአራት ቡድን በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች ከቤት ንብረታቸው የተፈናቀሉ ዜጎችን ከዛሬ ጀምሮ በመጎብኘት ላይ ናቸው።

የግጭት አደጋ የደረሰበት ተሽከርካሪም የዚሁ አካል ሲሆን አራት የምክር ቤት አባላትን ይዞ ሲጓዝ ነው ሸኖ አካባቢ የነበሩበት ሎንግ ቤዝ መኪና ከሃይሉክስ ጋር ተጋጭቶ አደጋ ያጋጠመው።

በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል የድንገተኛና የመጀመሪያ ጽኑ ህሙማን ህክምና ክፍል ረዳት ፕሮፌሰር ተመስገን በየነ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንደገለጹት አራት የምክር ቤት አባላት የመኪና አደጋ ደርሶባቸው በሆስፒታሉ ህክምና ተደርጎላቸዋል።

ሁለቱ ቀላል የመላላጥ ጉዳት የደረሰባቸው ሲሆን ሁለቱ ላይ ደግሞ ከበድ ያለ ጉዳት መሆኑን አስታውቀዋል።

ከቀላል ማስታገሻ ጀምሮ የአንገት በላይና የሲቲስካን ምርመራ እንደተደረገላቸውና ተከታታይ ህክምና እንደሚሰጣቸውም አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም