ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ የ10 አገር አምባሳደሮችን የሹመት ደብዳቤ ተቀበሉ

67

አዲስ አበባ  መጋቢት 19/2011 የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ የ10 አገር አምባሳደሮችን የሹመት ደብዳቤ ዛሬ ተቀበሉ።

ፕሬዚዳንቷ የተቀበሉት ከአፍሪካ፣ ከእስያ (መካከለኛውና ሩቅ ምስራቅ)፣ አውሮፓ፣ ደቡብ አሜሪካ እና አውስትራሊያ አህጉር የተወከሉ አምባሳደሮችን ሹመት ደብዳቤ ነው።

በዚህ መሰረትም የጃፓን፣ ናሚቢያ፣ አውስትራሊያ፣ ብራዚል፣ ቦትስዋና፣ የተባበሩት አረብ ኢምሬቶች፣ ብሪታንያ፣ ቺሊ፣ የአንጎላ እና የላቲቪያ አምባሳደሮች ለፕሬዚዳንቷ የሹመት ደብዳቤያቸውን አቅርበዋል።

አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የጃፓን፣ ቦትስዋና እና ብሪታኒያ አምባሳደሮች የአገራቸውንና የኢትዮጵያን ሁለትዮሽ ግንኙነቱን ይበልጥ ለማጠናከር እንደሚሰሩ ተናግረዋል።

የጃፓን አምባሳደር ሚስተር ዳቱሱጌ ማሱንጋ፤ አገራቸው ከኢትዮጵያ ጋራ ያላትን ጠንካራ ወዳጅነት ለማጠናከር እንደሚሰሩ ገልጸዋል።

በተለይም በትምህርት፣ በንግድ፣ ኢንቨስትመንትና በባህል ልውውጥ መስኮች ትኩረት ሰጥተው እንደሚሰሩ ተናግረዋል።

የቦትስዋናው አምባሳደር ሚስተር ዜኒን ሲኖምቤ በበኩላቸው፣ በተለያዩ መስኮች ትብብር ያላቸው ኢትዮጵያና ቦትስዋና ጠንካራ ወዳጅነት እንዳላቸው ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ በሳምንት አምስት ጊዜ ወደ ቦትስዋና በረራ ማድረጉ የወዳጅነቱ ማሳያ እንደሆነም አስረድተዋል።

በእንስሳት ሀብት፣ በሰው ሃብት ልማት፣ በህግ ጉዳዮች፣ በፀረ ሙስና ትግልና በመልካም አስተዳደር ዘርፎች በጋራ ለመስራት ዝግጁ መሆናቸውን አመልክተው ሁለቱን አገሮች ተጠቃሚ ለሚያደርጉ ጉዳዮች ትኩረት ሰጥተው እንደሚሰሩ ጠቁመዋል።

የብሪታንያ አምባሳደር ዶክተር አላስቲር ዴቪድ ሚፒል አገራቸው በኢትዮጵያ እየተካሄደ ያለውን የድህነት ቅነሳ ተግባር እያገዘች መሆኑን አስታውሰዋል።

ብሪታንያ ከኢትዮጵያ ጋር በልማት ሥራዎች የነበራት ወዳጅነትን የበለጠ በማጠናከር በፖለቲካ፣ ወታደራዊ እና በሌሎች ዘርፈ ብዙ ጉዳዮች በጋራ መስራት እንደምትሻ አመላክተዋል።

ኢትዮጵያ በምስራቅ አፍሪካ ሰላምና ፀጥታ ለማስፈን የምታደርገውን ጥረት አድንቀው ለአብነትም በቀጠናው ሰላም ለማስከበር ያሰማራችውን የሰላም አስከባሪ ኃይል ጠቅሰዋል።

በኢትዮጵያ እየተካሄደ ያለውን የዴሞክራሲ ሽግግር እንዳስደነቃቸው እና ለውጡን በቅርበት እንደሚከታተሉት ጠቁመዋል።

የሹመት ደብዳቤያቸውን ያቀረቡት አምባሳደሮች በኢትዮጵያ እየተካሄደ ያለውን የለውጥ ሂደት እንደሚደግፉ እና ለውጡ ለቀጠናው አገሮች ብሎም ለአፍሪካ ትልቅ ጠቀሜታ ያለው በመሆኑ ለውጡን ለመደገፍ ያላቸውን ዝግጁነት ገልፀዋል።

ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ በበኩላቸው፤ ከአገሮቹ ጋር በፖለቲካው መስክ ያለውን ጠንካራ ግንኙነት ወደኢኮኖሚ መስክ ለማሸጋገር ይሰራል።

ኢኮኖሚያዊ ግንኙነቱን ለማሳደግ በንግድ እና ኢንቨስትመንት ዘርፎች መስራት እንደሚገባ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ለአምባሳደሮቹ መግለፃቸውን ውይይቱን የተከታተሉት የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር ምክትል ቃል አቀባይ አቶ አበበ መብራቱ ለኢዜአ ተናግረዋል።

ፕሬዚዳንቷ፤ የኢትዮጵያ አየር መንገድ በየአገሮቹ የሚያደርጓቸውን በረራዎች በመጠቀም ኢኮኖሚያዊ ግንኙነቱን የበለጠ ማሳደግ እንደሚገባ እና ቀደም ሲል የተፈረሙ ስምምነቶችን ስራ ላይ ለማዋል እንዲሰሩ ጭምር ጠይቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም