የዴሞክራሲ ተቋማት እንዲጠናከሩ በትኩረት መስራት እንደሚገባ ምክር ቤቱ አሳሰበ

42

ባህርዳር መጋቢት 19/2011 የዴሞክራሲ ተቋማት እንዲጠናከሩ አመራሩ የሰራተኞችን አቅም መገንባትና አመለካከት ላይ በትኩረት መስራት እንዳለበት የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አሳሰበ።

በምክር ቤቱ የህግ፣ ፍትህና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የህዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም ባህርዳር ቅርንጫፍ የስራ አፈጻጸምን ገምግሟል።

የቋሚ ኮሚቴው ቡድን መሪ አቶ ጥላሁን ጂግሳ በዚህ ወቅት እንዳሉት ቅርንጫፉ ስራዎችን በእቅድ በመመራትና በመፈፀም፣ በሪፖርትና ግብረ መልስ አሰጣጥ በኩል ያከነወነው ተግባር  በጥንካሬ የሚታይ ነው።

ተቋማዊ ራዕይና ተልዕኮን ከማሳካት አንጻር የቅርንጫፉ  አመራሮችና ሰራተኞች ተናቦ በመስራት በኩል ክፍተች እንዳሉ  ከሰራተኞች ጋር ካደረጉት  ውይይት  መረዳታቸውን አመልክተዋል፡፡

የህዝብ እንባ ጠባቂ ተቋምንና የሰብአዊ መብት ኮሚሽንን ተግባርና ኃላፊነት ቀላቅሎ መመልከት በሰራተኞች እንደሚስተዋል መታዘባቸውን ጠቁመዋል።

"ለሰራተኞች የአጭርና የረጅም ጊዜ ስልጠና በመስጠት አቅማቸውን በመገንባት በኩል የተሄደበት ርቀት ውስንነት ያለበት ነው" ያሉት ቡድን መሪው  ይህም በቀጣይ ሊስተካከል እንደሚገባ አሳስበዋል።

የህዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም ባህርዳር ቅርንጫፍ  ሰራተኞችን አቅም በመገንባትና አመለካከታቸውን ወደ አንድ በማምጣት ረገድ አመራሩ በቀጣይ በትኩረት መስራት እንዳለበት አስገንዝበዋል።

የቅርንጫፉ እንባ ጠባቂ አቶ ጋሻነው ደሴ በበኩላቸው ከህብረተሰቡ ከ150 ሺህ በላይ ቅሬታዎች መቅረባቸውን ገልጸዋል።

የቀረቡ ቅሬታዎችን በአስተዳደራዊ መንገድ ለመፍታት ጥረት እየተደረገ መሆኑን ጠቅሰው በየደረጃው ያለው አመራር ተባባሪ አለመሆን  ስራው በሚፈለገው  ልክ እንዳይከናውን ማድረጉን አመልክተዋል።

የቅርንጫፉ አመራር ስራዎችን ከሰራተኛው ጋር ተናቦ እየሰራ መሆኑን ያስረዱት አቶ ጋሻነው  የበጀትና የተሽከርካሪ ዕጥረት ችግር እንደሆነባቸው ተናግረዋል።

" በሰራተኛው በኩል የአጫጭርና የረጅም ጊዜ ስልጠናዎች አይሰጡንም ተብሎ የተነሳው ጥያቄ ትክክል እንዳልሆነና በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ስልጠና በመስጠት የሰራተኞች አቅም እየተገነባ ነው " ብለዋል። 

ቅርንጫፉ ኃላፊነቱን መወጣት እንዲችል የተሽከርካሪና የበጀት እጥረት ችግሩ እንዲፈታ ቋሚ ኮሚቴው የበኩሉን ጥረት እንዲያደርግ ጠይቀዋል።

ምክር ቤቱም የዴሞክራሲ ተቋማት እንዲጠናከሩና የሚስተዋሉ የግብዓት አቅርቦት ችግሮች እንዲፈቱ የጀመረውን የክትትልና የድጋፍ ስራ አጠናክሮ እንደሚቀጥል የቋሚ ኮሚቴው ቡድን መሪ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም