በአዋሳኝ አካባቢዎች የሚስተዋሉ የጸጥታ ችግሮችን በጋራ እንፈታለን... የአማራና የኦሮሚያ ክልሎች

65

ባህዳር መጋቢት 19/2011 በአማራና ኦሮሚያ ክልሎች አዋሳኝ ቦታዎች የተከሰቱ ግጭቶችን በዘላቂነት ለመፍታት የጋራ ኮሚቴ ተዋቅሮ ወደ ስራ መገባቱን የሁለቱም ክልሎች የፀጥታ ኃላፊዎች ተናገሩ።

ጉዳዩን አስመልክቶ ዛሬ የሁለቱም ክልሎች የፀጥታ ኃላፊዎች በባህርዳር የጋራ መግለጫ ሰጥተዋል።

የአማራ ክልል ሰላምና ደህንነት ቢሮ ምክትል ኃላፊ ኮሎኔል አለበል አማረ እንደገለጹት ሀገሪቱ በለውጥ ሂደት ላይ መሆኗን ተከትሎ መልካም የሆኑና ያልሆኑ ነገሮች እየተስተዋሉ ነው።

በዚህም በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች በሚከሰቱ የፀጥታ ችግሮች ህዝቦች ከቤት ንብረታቸው ሲፈናቀሉ ማስተዋል የተለመደ እየሆነ መምጣቱን ተናግረዋል።

በተለይም በአማራ ክልል ምንጃር ሸንኮራ ወረዳና በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ሸዋ ዞን አዋሳኝ ቦታዎች የተከሰቱ የፀጥታ ችግሮችን በጋራ ለመፍታት የሁለቱም ክልሎች የፀጥታ ቢሮዎች ተገናኝተው በመምከር ስምምነት ላይ መድረሳቸውን አስረድተዋል።

ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን፣ መፈናቀል እንዲቆምና የተፈናቀሉትም ወደ ነበሩበት እንዲመለሱ ለማድረግ የጋራ ኮሚቴ በማዋቀር ችግር ያለባቸውን አካባቢዎች የመለየት ስራ እያከናወኑ መሆናቸውን ገልጸዋል።

ለዘመናት ተዋልዶ የኖረውን የሁለቱ ክልል ህዝብ ዕርስ በዕርስ ሊያጣሉት ከሚጥሩ የፖለቲካ ነጋዴዎች የራሱን ሰላምና ደህንነት ነቅቶ ሊጠብቅ እንደሚገባም አሳስበዋል።

የህግ የበላይነት እንዲከበር፣ ዜጎች ከቦታ ቦታ ተዘዋውረው እንዲሰሩ ከኦሮሚያ ክልል በተጨማሪ በቀጣይ ከሌሎች አጎራባች ክልሎች ጋር በጋራ ለመስራት እንደሚጥሩም አስረድተዋል።

የኦሮሚያ ክልል ሰላምና ፀጥታ ጉዳዮች ቢሮ ምክትል ኃላፊ ኮሎኔል አበበ ገረሱ በበኩላቸው የሁለቱ ክልል ህዝቦች የረጅም ዘመናት የጋራ ባህልና እሴት የገነቡ ናቸው።

“ለውጡ እንዲመጣም ሁለቱ ክልሎች እጅ ለእጅ ተያይዘው ለአሁኑ ዕድል እንድንበቃ ያስቻሉን በመሆኑም ማንም ጥቅሙ የተነካበት የፖለቲካ ኮንትሮባንዲስት ህዝቦቹን የሚያጋጭበት ሁኔታ ሊኖር አይገባም” ብለዋል።

ለውጡን ለማስቀጠልና የበለፀገች ኢትዮጵያን በጋራ ለመገንባትም ሁለቱም ህዝቦች ከአሉባልታ ርቀው ለዘላቂ ሰላማቸው ዘብ ሊቆሙ እንደሚገባም አስገንዝበዋል።

“ዘላቂ ሰላማችንን ለማስጠበቅም በጋራ ተቀናጅተንና ተናበን አለመስራታችን ለፖለቲካ ነጋዴዎች ሰለባ እንድንሆን አድርጎናል” ብለዋል።

አሁን የተከሰቱ ችግሮችን ለመፍታትም በጋራ የተቋቋመው የፀጥታ ኮሚቴ የአጭር፣ የመካከለኛና የረጅም ጊዜ ዕቅዶችን አውጥቶ ወደ ስራ መግባቱን አስረድተዋል።

በቀጣይም የሀገሪቱን ሰላምና ፀጥታ ለማስከበርና ዘላቂ ሰላም በሀገሪቱ እንዲሰፍን ከሌሎች ክልሎች ጋር በጋራ እንደሚሰሩም ኃላፊዎቹ አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም