ትእምት በአፋርና ዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አባላት የሰማዕታት ቤተሰቦች ወርሃዊ የገንዘብ ድጋፍ እንዲደረግላቸው ወሰነ

81

መቀሌ መጋቢት 18/2011 የትግራይ መልሶ መቋቋም ተቋም /ትእምት/ የአፋርና ዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አባላት የሰማዕታት ቤተሰቦች ወርሃዊ የገንዘብ ድጋፍ እንዲደረግላቸው ወሰነ፡፡

የትእምት ባለ አደራ ቦርድ የበጎ አድራጎት ጽህፈት ቤት  ዳይሬክተር አቶ ጥላሁን ታረቀ ዛሬ እንደገለጹት የደርግን ስርዓት ለመጣል በተካሄደው የትጥቅ ትግል የአፋርና የዋግ ኽምራ  ብሄረሰብ አባላት ከህወሓት ጎን ተሰልፈው የህይወት መስዋእትነት ከፍለዋል።

ባለ አደራ ቦርዱ ከሰማዕታት ቤተሰቦች ለቀረበው ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት ወርሃዊ የገንዘብ ድጋፍ እንዲደረግላቸው ዛሬ ወስኗል፡፡

በትግራይ ክልል የሚገኙ 13 ሺህ 502 የሰማዕታት ቤተሰቦች በወር ይስጣቸው ከነበረው 450 ብር  650 ብር ከፍ እንዲል መወሰኑን ዳይሬክተሩ አስታውሰዋል።

በውሳኔው መሰረት የሁለቱም ብሔረሰብ አባላት የሰማዕታት ቤተሰቦችም እኩል እንዲሚከፈላቸው አመልክተዋል፡፡

በዚህም የአፋር ክልላዊ መንግስት የይሁንታ ምላሽ በመስጠቱ   200 ለሚደርሱ የሰማዕታት ቤተሰቦች ከሚያዝያ ወር 2011 ዓ.ም. ጀምሮ የድጋፉ ተጠቃሚ እንደሚሆኑ ዳይሬክተሩ ገልጸዋል፡፡

በአማራ ክልል ዋግ ኽምራ ዞን የሚገኙ የሰማዕታት ቤተሰብ አባላት የክልሉ መንግስት ይሁንታ ከሰጠ በኋላ የቤተቦቹ ብዛትና ሌሎች ዝርዝር ሁኔታዎች በጥናት ተለይቶ ክፍያ እንደሚፈጸም አስታውቀዋል፡፡

ትእምት በትግሉ ወቅት ለተሰው  ቤተሰቦች በዓመት ይመድበው የነበረውን  81 ሚልዮን ብር  ወደ 117 ሚልዮን ብር ከፍ ማድረጉን አስረድተዋል።

ተቋሙ ለታጋይ ሰማዕታት ቤተሰቦች የገንዘብ ድጋፍ ከማድረጉ በተጨማሪ በአማራ ክልል ሰቆጣ ከተማ በ22 ሚሊዮን ብር የቴክኒክ፣ሙያ ትምህርትና ስልጠና ኮሌጅ ህንጻ አስገንብቶ ባለፈው ዓመት ማስረከቡን አስታውሰዋል።

ትእምት ባለፉት ዓመታት ለማህበራዊ አገልግሎት መስጫ ተቋማት ግንባታ፣ለሰማዕታት ቤተሰቦች ድጋፍ፣በበጎ ስራ ለተሰማሩ የሀገር ውስጥ ምግባረ ሰናይ ድርጅቶች  ከ3 ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ ማድረጉም ተመልክቷል፡፡

የትግራይ ክልል ምክር ቤት በአምስተኛው ዘመን 15ኛ መደበኛ ጉባኤ የተቋሙን ተጠሪነት ለክልሉ ምክር ቤት እንዲሆን የቀረበለትን ሀሳብ  በሙሉ ድምጽ ማጽደቁ  ታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም